Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ልምዷን ለዓለም የጤና ድርጅት አባል አገሮች አካፈለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ያከናወናችውን ተግባራትና ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች ለዓለም የጤና ድርጅት አባል አገሮች አካፈለች።

ኢትዮጵያ ልምዷን ያካፈለችው ዛሬ የዓለም የጤና ድርጅት ጉባዔ ከአባል አገሮች ጋር ባካሄደው ጉባዔ ነው።

በጉበዔው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ ከ194 አገሮች የተወጣጡ የጤና ሚኒስትሮች ተሳትፈውበታል።

በቪዲዮ ኮንፈረንስ በመታገዝ በተከናወነው ጉባዔ ÷ ወረርሽኙን የተከላከለችው ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ሳታደርግና የቫይረሱ ስርጭት የከፋ ጉዳት መከላከሏን ለተሳታፈዎቹ አስረድታለች።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ÷ኢትዮጵያ ድርጅቱ በሽታውን ዓለም አቀፍ ስጋት ብሎ ከማወጁ ቀደም ብላ የጥንቃቄ ስራዎችን መጀመሯን ተናግረዋል።

አገሪቷ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ መንገደኞች መተላለፊያ ማዕከል አንደመሆኗ መጠን ጥብቅ የመግቢያና መውጫ ልየታ መጀመሯንም ለአብነት አንስተዋል።

ከዚያም ባለፈ የተለያዩ ሚኒስትሮችን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮም የለይቶ ማቆያዎችንና የሕክምና መከታተያ ጣቢያዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።

ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላም ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና ከውጭ የሚመጡ ግለሰቦች በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያዎች እንዲገቡ መወሰኑን ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከሚያዝያ 8 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ታውጆ ሙሉ ለሙሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሳይገደብ የጥንቃቄ አቅጣጫዎችን ተፈጻሚ መደረጋቸውንም  ነው የተናገሩት።

ከዚም ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ ምንም የምርመራ አቅም ካልነበረበት ሁኔታ አሁን ላይ አገልግሎት የሚሰጡ 38 የመመርመሪያ ጣቢያዎችን በአጭር ጊዜ ማቋቋም ተችሏል ብለዋል።

ሌሎች ተጨማሪ ላቦራቶሪዎችም በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ዕለታዊ ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ድርስ 227 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ምርመራ መደረጉንና ይህም ከአፍሪካ አራተኛ ደረጃ የሚይዝ የምርመራ አፈጻጸም መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን ካለን ሰፊ የሕዝብ ቁጥር አንጻር አሁንም በስፋት መስራት እንዳለብን እንገነዘባለን ብለዋል።

በርዕሰ መዲናዋ አዲስ የተገነባ ሆስፒታልና ትልቁን የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶላቸው ለቫይረሱ ምላሽ ስራ አንዲውሉ  መደረጉንም አንስተዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሚመራው ጤና ምላሽ ሥራም 12 ከሚሆኑ የጤና ዘርፍ የሙያ ማህበራትና በውጭ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አማካሪ ቡድንን ያሳተፈ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው÷የግሉ ዘርፍም በሥራው እንዲሳተፍ ተደርጓልም ነው ያሉት ዶክተር ሊያ።

የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል በተጓዳኝ እንደ ህጻናትና እናቶች ጤና ያሉ መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት እንዳይቋረጡ ሰፊ መሰራታቸውንም ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ የወባ፣ የቢጫ ወባ፣ የኩፍኝና ኮሌራ ወረርሽኞች ተከስተው እንደነበርና ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንደተቻለም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሟላ ግብዓት ያላቸው የለይቶ ማቆያዎች እጥረት መከሰቱን ገልጸዋል።

የቫይረሱ መከላከያ ግብዓቶች እጥረትና በኢትዮጵያ የተጠለሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ አገሮች መኖራቸውም ኢትዮጵያ መሻገር ያለባት ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑንም ዶክተር ሊያ አስረድተዋል።

የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመከላከል እያደረጉት ያለውን ተጋድሎም ”እጅግ የሚያኮራ” በማለት ለተሳታፊዎቹ  መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.