Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 77ኛ መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

የመንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ረቂቅ አዋጅ ዋና ዓላማ የመንግስት አካላት በመንግስት ፕሮጀክቶች ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት በግልፅ በማመላከት ተጠያቂነትን እና ግልፀኝነትን በማስፈን የፕሮጀክቶችን ውጤታማነት ማጎልበት እንደሆነ ተመልክቷል።

በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የመንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ስርዓት ባለመኖሩ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ወጪ እና ጥራት ባለመጠናቀቃቸው የሀገሪቱን ውስን ሃብት ለከፍተኛ ብክነት እየዳረጉ ይገኛሉም ነው የተባለው።

በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ወጥ የሆነ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓትን በህግ ለመደንገግ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ልኳል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በውጭ ሀገራት ስለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠትና የመፈፀም ስምምነትን ለማፅደቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅንም ተመልክቷል።

በውጭ ሀገራት ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ ማጽደቋ የውጭ ባለሃብቶችን ስጋት የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ የውል አፈጻጸሞችን ቀልጣፋ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

ወደ ሀገሪቱ የሚኖረው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር የስምምነቱ መጽደቅ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ስምምነቱን ለማፅደቅ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በረቂቆቹ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረቡትን የተለያዩ ስምምነቶች እና የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል አዋጆቹ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ማእድን፣ ነዳጅ እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል።

ረቂቅ ደንቡ በአሁኑ ወቅት ለማዕድንና ነዳጅ ሃብት መንግስት የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ በሂደት የታዩ ክፍተቶችን የሚሞሉ ተግባሮችን አካቶ እንዲሰራ እና አደረጃጀቱም ይህንኑ በሚያግዝ መልኩ እንዲደራጅ ለማድረግ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንቡን አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ማቅረቡ የተመለከተ ሲሆን፥ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ማስተካከያዎችን በማከል በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.