Fana: At a Speed of Life!

“የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ” እንዲቋቋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ”የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ” እንዲቋቋም ውሳኔ አሳለፈ።

የኤጀንሲው መቋቋም በተያዘው ዓመት በሰፊው የተሰራውን የትምህርት መሳሪያዎች አቅርቦትና የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ቀጣይነት እንዲኖረው እና ተቋማዊ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ኤጀንሲው በየዓመቱ ለተማሪዎች የሚደረጉ የቁሳቁስ ድጋፎች እና የምግብ አቅርቦቶችን በተቀናጀና ወጥ በሆነ መልኩ እንዲሁም ያለመቆራረጥ ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።

ለዚህም ኤጀንሲው የከተማ አስተዳደሩ ለተግባሩ የመደበውን በጀት ስራ ላይ ከማዋል ጀምሮ ለጋሽ አካላትንና በጎ ፈቃደኞችን የማስተባበርና አቅርቦቶቹ በትክክል እየተዳረሱ መሆኑን የሚቆጣጠር ይሆናል።

አስተዳደሩ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ለታዳጊ ሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ የማሰራጨት እቅድም በኤጀንሲው የሚመራ መሆኑ ተመላክቷል።

የኤጀንሲው መቋቋም ታዳጊዎች ትኩረታቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲሆን በማድረግ በታዳጊዎች የትምህርት አቅም ላይ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

በሌላ በኩል ተማሪዎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም በውጪም ይሁን በሀገር ውስጥ የነጻ ትምህርት እድል እንዲያገኙ የማድረግ ተግባርን የሚያከናውን ይሆናል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባደረገው መደበኛ ስብሰባም ኤጀንሲው እንዲቋቋም የቀረበውን አዋጅ ለምክርቤት መርቷል።

ኤጀንሲው ተጠሪነቱ ለከንቲባ ጽህፈት ቤት እንዲሆን መወሰኑንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለተያዘው የትምህርት ዘመን በከተማ አስተደዳሩ አነሳሽነት ለ600 ሺህ ተማሪዎች ዩኒፎርም ደብተርና የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ፥ከ300 ሺህ በላይ ታዳጊ ተማሪዎች ደግሞ የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.