Fana: At a Speed of Life!

“ከውሃ ሙሌት መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ የተደረገ ስምምነት የለም፤ እለቱ ሲደርስ ታዩታላችሁ”- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ የተደረገ ስምምነት እንደሌለ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ።

በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዌቢናር /በቪዲዮ ኮንፍራንስ አካሂደዋል።

በፕሪቶሪያ የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና በደቡባዊ አፍሪካ የኢትዮጵያ ምሁራን ማህበር ትብብር አዘጋጅነት በተካሄደው ዌቢናር ላይም በደቡብ አፍሪካ፣ ሞዛምቢክ፣ ናምቢያ፣ ቦትስዋና፣ ሌሴቶ፣ ኢስዋቲኒ እና ማዳጋስካር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል።

በዌቢናሩ ላይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከቱ ጉዳዮች፣ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ለቀጠናው ሃገራት የሚኖረው ፋይዳ፣ የናይል ወንዝ ለዘላቂ ትብብር ለአህጉራዊና አለማቀፍ ግንኙነት እንዲሁም የኢትዮጵያ የውሃ ኃብትና አለማቀፍ ግንኙነት ላይ ትኩረት በማድረግ ምክክር ተካሂዶባቸዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለዌቢናሩ ተሳታፊዎች የህዳሴ ግድብ ግንባታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል፣ በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር እንዲሁም ወደ ፊት ምን ማድረግ ይጠበቅብናል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜም የዌቢናሩ ተሳታፊዎች ከግድቡ ድርድር ጋር በተያያዘ እንዲሁም በትናንትናው እለት የአፍሪካ ህብረት አባላት ቢሮ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ልታራዝም ነው በሚል በተሰራጨው ዘገባ ዙሪያ ለዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጥያቀዌ አቅርበዋል።

በዚህም ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፥ በትናንትናው እለት የተካሄደው ውይይት እና ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል ወደ አፍሪካ መመለሱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል መሆኑን አብራርተዋል።

ትናንት በተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት በሂደት ላይ ስለሆነች ቀደም ብሎ ሌሎች የቴክኒክ ባለሙያዎች ተጨምረውበት ስምምነቱ ይለቅ የሚል ላይ ተመክሯል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህንን ጉዳይ የግብፅ እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ነገሩን አጣመው ለራሳቸው በሚመች መንገድ ነው የፃፉት ሲሉም ገልፀዋል።

“የግድቡን ውሃ ሙሌት ለማራዘም ተስማምታለች የሚለው የሌለ ነገር ነው፤ ትናንት መሪዎች ናቸው የተወያዩት እንጂ ስምምነት አልተደረገም” ሲሉም አረጋግጠዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ አክለውም፥ “ከውሃ ሙሌት መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ ምንም ብዥታ የለም፤ ሁሉም በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል፤ እለቱ ሲደርስ ታዩታላችሁ” ሲሉም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን ከግድብ ግንባታዋ አንድም ሰከንድ የሚያቋርጣት የለም ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፥ በአሁኑ ሰዓት ውሃ የመያዝ፣ የግድቡን ተርባይኖች የመትከል እና የመሳሰሉት ዝርዝር ስራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

ውይይቱን ተከትሎም በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የአቋም መግለጫ ያወጡ ሲሆን፥ በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ከፍተኛ ተሳትፎና ተነሳሽነት እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኝነት የራሳችን አሻራ ያረፈበት በራሳችን ሃብት ብቻ የሚገነባ የኢትዮጵያውያን አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በእጅጉ የተንጸባረቀበት የብሄራዊ ኩራታችን መገለጫ ግድባችን ነው ብለዋል።

ስለሆነም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ህብረታችንና አንድነታችን በማጠናከር በጽናትና በቁርጠኝነት በመቆም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በሙያ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የአድዋን ድል በዘመናችን ለመድገም ቃል እንገባለን ሲሉም ገልፀዋል።

አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ከቅኝ ግዛትና ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ባደረጉት መራራና የተራዘመ ትግል ኢትዮጵያ የማይተካና ጉልህ አወንታዊ ሚና ማበርከቷን በማስታወስ፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን ጥቅም ላይ ለማዋል ሉዓላዊና ተፈጥሮአዊ መብቷን ለማስከበር በምታደርገው ጥረት አፍሪካውያን በሙሉ ፍትሃዊ አቋም ከያዘቸው ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.