Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የልማት እቅድ አዘገጃጀትና አቀራረብ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በጋምቤላ ክልል የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የልማት እቅድ አዘገጃጀትና አቀራረብ መመሪያ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ ካሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴኩዌይ ጆክ የልማት እቅድ የአንድን ሃገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት በተቀላጠፈና በተቀናጀ መልኩ ለመምራትና ለማስተዳደር የሚያስችል የተግባር መሳሪያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በክልላዊና በሀገራዊ ራዕይ መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖርና በዝግጅት ወቅትም በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተግባራዊ የሚደረጉ ወጥነት ያላቸው የእቅድ ዝግጅት ሂደቶችን ተከትሎ መዘጋጀት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የረጅምና የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ስኬታማ እንዲሆን በአፈጻጸም ሄደቱ ላይ ክትትልና ግምገማ ማድረግ ለታለመው ግብ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ከወዲሁ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ፡፡

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የመረጃና እቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ አበበ ጤናው የውይይት ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የክልሉ መንግስት ሊያሳካቸው የሚያልመውን የልማት ግቦችን በረጅም መሪ ዕቅድ አማካኝነት መምራት ለግቦቹ መሳካት አይነተኛ ሚና አለው፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የረጅምና የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ሲዘጋጅ ለአመራሩም ሆነ ለባለሙያው ግልጽ እንዲሆን ተደርጎ መዘጋጀት አለበት ያሉ ሲሆን ÷በዕቅድ ዝግጅቱ ወቅት የስራ ተመጋጋቢነት ያላቸው መስሪያ ቤቶች ተቀናጅተው በማቀድና በመተግበር የመንግስትና የህዝብ ሃብት እንዳይባክን ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ መናገራቸውን ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.