Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው በተቋማት የሚበለጽጉና መሰረታቸዉን ኢንተርኔት ላይ ያደረጉ ሲስተሞች ከትግበራ በፊት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ፍተሻ መደረግ እንደሚገባቸዉገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲበተቋማት የሚበለጽጉና መሰረታቸዉን ኢንተርኔት ላይ ያደረጉ ሲስተሞች ከትግበራ በፊት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ፍተሻ መደረግ እንደሚገባቸዉ ገለጸ።

ተቋማት የሚያበለፅጓቸው መሰረታቸዉን በይነ-መረብ ላይ ያደረጉ ሲስተሞች /web-based systems/ አገልግሎት መስጠት ከመጀመራቸዉ በፊት በሚመለከታቸዉ ባለሙያዎች የደህንነት ተጋላጭነታቸዉ ተፈትሾ ሊስተካከል እንደሚገባልም ነው ያለው ኤጀንሲው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ከፍያለው ተፈራ ÷ ተቋማት የሚጠቀሙባቸዉን የሶፍትዌር ሲስተሞችን (አፕሊኬሽኖችን) በተለይም ደግሞ ዌብ ቤዝድ ሲስተሞችን (ድረ ገፆችን) መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት በሚመለከታቸዉ ባለሞያዎች የደህንነት ተጋላጭነታቸዉ ተፈትሾ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ ጥቃቶች የቴክኖሎጂዉ እና የአሰራር ስርዓት ተጋላጭነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ አብላጫዉ ተጋላጭነት በሰዉ ሀይል ጥንቃቄ ጉድለት፣ የአጠቃቀም ግንዛቤ ማነስ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈጠር ችግር የሚከሰት መሆኑን  ተናግረዋል።

ሃላፊው አያይዘውም  ዘጠና በመቶው ተጋላጭነት በተጠቃሚዉ (የሰዉ ሀይል) የሚመጣ በመሆኑ ተቋማት ለሰዉ ሃይላቸዉ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ግንዛቤ መስጠት እና የአሰራር ስርዓታቸዉን ቀጣይነት ባለዉ መልኩ እየፈተሹ ሊያሻሻሉ ይገባልም ነው ያሉት።

የሰሞኑ ከግብጽ የተነሳዉ የሳይበር ጥቃት የተለየ የፖሊቲካ ፍላጎት መሰረት አድርጎ የተፈፀመ መሆኑን እና በዓለማችን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ከግብፅ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የተለያዩ ሀገሮች የሚሲነዘሩ መሰል የሳይበር ጥቃቶች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ኢመደኤ የትኛዉንም ዓይነት የሳይበር ጥቃቶች በዉስጥና ከዉጪ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመመከት ስራ ሲሰራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ከፍያለው በተለይ የመንግስት ቁልፍ ተቋማትን በልዩ ትኩረት ሊኖርባቸዉ የሚችሉ ተጋላጭነቶችን ችግሮች ከመከሰታቸዉ በፊት እየተፈተሸ የሚገኙ ክፍተቶች እንዲደፈኑ በመደረጉ የሰሞኑ የሳይበር ጥቃቶች የከፋ አደጋ ሳያስከትሉ እንዲከሽፉ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከዚያም ባለፈ ኤጀንሲው በፊት ከነበረዉ በተሻለ መልኩ በዉስጥ ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ጥምረት በመፍጠር የተለያዩ ስራዎችን የሰራ ሲሆን በቀጣይም ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የሳይበር ጥቃቱ ከግዜ ወደ ጊዜ በረቀቀ መልኩ የሚፈፀምና የጥቃቱ መጠንም እየጨመረ ሊመጣ እንደሚችል ስጋታቸውን የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ ቁልፍ በሆኑ የመንግስት ተቋማት (በፋይናንስ እና በኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ) የተሰማሩ ባለሙያዎች ከኤጀንሲያችን ጋር እንደ ከዚህ በፊቱ ቅንጅታችንን በማጠናከር ሊመጣ ለሚችለዉ ማንኛዉም አይነት የሳይበር ጥቃት የተለየ ትኩረት እና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሁላችንም ክብርና መመኪያ በመሆኗ ባለን አቅም ሁሉ በተለይ ደግሞ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ለሃገራችን ማበርከት የምንችላቸዉን ድጋፎች ማበርከት እንዳለብን  እና የአንድ ሀገር የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የአንድ ተቋም ወይም የተወሰኑ ሀላፊዎች ሃላፊነት ብቻ ሊሆኑ አይችሉም ብለዋል።

ሃላፊው አክለውም  ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ባለበት ቦታ ባለዉ አቅም እና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት መጠን ለሃገሩ የበኩሉን ማበርከት ይኖርበታል ሲሉ መክረዋል።

ስለሆነም ሳይበር ደህንነቱም ዘርፍ ሊሰነዘር የሚችለዉ ጥቃት አለማቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን በየትኛዉም የአለማችን ጫፍ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸዉ ላይ ሊሰነዘር የሚችለዉን ጥቃት በመመከቱ ሂደት የዜግነት ግዴታቸዉን እንዲወጡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አደራ ማለታቸውን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.