Fana: At a Speed of Life!

የዳቦ ስንዴን ከውጭ በግዥ የማስገባት ሂደት እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የሚታየውን የዳቦ ስንዴ እጥረት ለመቅረፍ መንግስት ስንዴን ከውጭ የማስገባቱን ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ እየተመረተ ያለው የዳቦ ስንዴ ከፍላጎቱ ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት መንግስት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በግዥ ከውጭ እያስገባ ይገኛል።

የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ስንዴን ከውጭ የማስገባቱ ሂደት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ እሸቴ አስፋው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የዳቦ ስንዴ ስርጭት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው የግዥ ሂደቱም መቆራረጥ እንደማይታይበት ተናግረዋል።

በየወሩም መንግስት በግዥ 650 ሺህ ኩንታል ስንዴ እያስገባ መሆኑንም አንስተዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ከዚህ ባለፈም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ እርምጃዎች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች እየተወሰዱ ይገኛል ብለዋል።

አሁን የመኸር ወቅት እንደ መሆኑ ከሀገር ውስጥ ምርት በመግዛት ለአርሶ አደሩ እና ለሸማቹ እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስርዓት ለመዘርጋት የኢትዮጵያ ንግድ ስራ ኮርፖሬሽን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑንም አስረድተዋል።

ግብርናውን ማዘመን በተለይም ሰፋፊና ቆላማ አካባቢዎችን በማልማት በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት አመታት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሃገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በስላባት ማናዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.