Fana: At a Speed of Life!

ከሰሞኑ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር ውሎ መረጋጋት መፈጠሩን መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሰሞኑ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር ውሎ መረጋጋት መፈጠሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢዜአ መግለጫ ሰተዋል።

የሰላም መደፍረሱ ባጋጠማቸው አካባቢዎች የፀጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመናበብ ችግሩን ለመወጣት መስራታቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በቅንጅት በመስራታቸው ለተመዘገበው ውጤትም ምስጋና አቅርበዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ወደ ፍትህ አደባባይ የሚወጡበት ስርዓት በአግባቡ እየተመራ መሆኑን እና ምርመራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የተፈጠረውን ግጭት የማረጋጋት፣ ዜጎችን የማቋቋምና የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ እንደገና ብጥብጥና ረብሻ እንዲነሳ ጥሪ የሚያስተላለፉ አካላት እንደነበሩ አንስተዋል።

“ጥሪው ቢተላለፍም ህብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር የአመጽ ጥሪዎቹ እንዲከሽፉ አድርጓል” ብለዋል።

“አሁን የምንገኝበት ምዕራፍ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የምንረባረብበት ነው” ያሉት አቶ ንጉሱ፤ የብልጽግና ጉዞ አንዱ ቁልፍ አጀንዳ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሆኑን ገልፀዋል።

የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚደረግን ሴራ ህዝቡ በአንድነት ቆሞ እዳከሸፈው ተናግረው፤ ኢትዮጵያ እንድትዳከምና በድህነት ውስጥ እንድትቆይ የሚፈልጉ ወገኖች እንዳሉ ገልጸዋል።

የእነዚህ ወገኖች ተላላኪ የሆኑ ቡድኖች አገሪቱን ለማተራመስና ለማፍረስ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ቢጠቀሙም መንግስትና ህዝብ በአንድነትና በጋራ ቆመው እንደሚመክቱት ነው የተናገሩት።

በህብረተሰቡ ሲነሳ የነበረው “የህግ የበላይነት ይከበር” ጥያቄ ላይ መንግስት ብዥታ ኖሮት ሳይሆን የዴሞክራሲ ምህዳር እንዲሰፋ መደማመጥና በሃሳብ መታገል እንዲሰፋ በሚል የታገሰው መሆኑን ተናግረዋል።

በግጭት ምክንያት የሚጠፋ ሀብትና ንብረት እንዳይኖር መንግስት ከልክ በላይ መታገሱን ህዝቡ እንደሚገነዘብ ያነሱት አቶ ንጉሱ፤ አሁን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኝነት እንዳለ ገልጸዋል።

በዚህም በየትኛውም አካባቢ ያሉ ህገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር እንዲሆኑ መደረጉን እና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ህብረተሰቡን በማበጣበጥ ኢትዮጵያን በማዳከምና በማፍረስ ለባዕዳን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ዓላማ በህዝብና መንግስት ትብብር የሚከሽፍ መሆኑን ነው ያሰመሩበት።

ሰሞኑን በደረሰው ጉዳት ከቤታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ዜጎችን መደገፍና መርዳት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.