Fana: At a Speed of Life!

የጉራጌ ዞን እና የስልጤ ዞን ተወላጆች የዘንድሮውን የዒድ አል-አድሃ ዓረፋ በዓል ባሉበት እንዲያከብሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጉራጌ ዞን እና የስልጤ ዞን ተወላጆች የዘንድሮውን የዒድ አል-አድሃ ዓረፋ በዓል ባሉበት እንዲያከብሩ የሁለቱ ዞን አመራሮች ጥሪ አቀረቡ።

ከትውልድ አካባቢያቸው ርቀው የሚገኙ የሁለቱ ዞን ተወላጆች የእስልምና እምነት ተከታዮች የዒድ አል-አድሃ ዓረፋ በዓልን ለማክበር ከያሉበት ወደ ቤተሰቦቻቸው ያቀናሉ።

ሆኖም የዘንድሮው የዒድ አል-አድሃ ዓረፋ በዓል እንደ ሁልጊዜው እንዳይከበር የኮሮና ቫይረስ ስጋት ሆኗል።

የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል፤ የእምነቱ ተከታዮች እና የዞኑ ተወላጆች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል በዓሉን በያሉበት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀረበውን ጥሪ ተላልፈው በዓሉን ለማክበር ወደ ዞኑ የሚመጡ ካሉ ግን የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ቆይታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ህብረተሰቡ እንደማይቀላቀሉ ተናግረዋል።

የስልጤ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙህዲን ሙኒር በበኩላቸው÷ የፊታችን ሐምሌ 23 ወይም 24 የሚከበረው ዓረፋ በዓልን በቀጣይ ዓመታት ከቤተሰብ ማንም ሳይጎድል በደመቀ ሁኔታ ማክበር እንዲቻል አሁን የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት ሁሉም የዞኑ ተወላጅ በያሉበት ማክበር አለባቸው ብለዋል።

በጥበበስላሴ ጀንበሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.