Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አመት የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማውን ደስታ በመግለፅ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ፓርቲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ክብርና ጥቅም ላይ የማይደራደር መሆኑን ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ራዕይ እውን የሚሆነው በብልፅግና መንገድ ብቻ እንደሆነ በፅናት የሚያምን እና ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚተጋ ፓርቲ በመሆኑ በተገኘው ስኬት እንኮራለን ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።

የብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የደስታ መግለጫ

ብልፅግና ፓርቲ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አመት የውሃ ሙሊት በስኬት መጠናቀቅ የተሰማውን ደስታ በመግለፅ ለመላ የሀገራችን ህዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ ይላል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ በታታሪና ቆራጥ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ በአለም ፊት ደምቃ የታየችበት የድል ቀን ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ባለቤቶች እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ የሀገር መሪዎች፣ የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች፣ የትምህርትና እምነት ተቋማት፣ በአጠቃላይ ሁሉም ዜጎች ደማቅ አሻራቸውን አሳርፈውበታል፡፡ በጉባ በረሃ ሌት ተቀን የሚሰሩ ባለሙያዎችና የሰራዊት አባላት በየእለቱ ታሪክ ፅፈውበታል፡፡ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእውቀት፣ በጉልበት፣ በገንዘብ የየራሳቸውን አሻራ ያሳረፉበት እንደመሆኑ መጠን የመጀመሪያው አመት የውሃ ሙሊት በስኬት መጠናቀቅ ለሁላችንም ብሄራዊ ኩራት እንድንጎናፀፍ ያስቻለን የድል ብስራት ነው፡፡

ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ክብርና ጥቅም ላይ የማይደራደር፤ የኢትዮጵያ ራዕይ እውን የሚሆነው በብልፅግና መንገድ ብቻ እንደሆነ በፅናት የሚያምን እና ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚተጋ ፓርቲ በመሆኑ በተገኘው ስኬት እንኮራለን፤ ይህን ድል ጠብቀን ሌሎች ብዙ ድሎችን ለማስመዝገብም እንደምንተጋ በዚሁ አጋጣሚ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ቃላችንን እናድሳለን፡፡

በሀገራችን የተመዘገበው ለውጥ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስም እጅግ አስፈላጊ እና የሚቻልም እንደሆነ በበርካታ ማሳያዎች እያረጋገጠ መጥቷል፡፡ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ አመት የውሃ ሙሊት ከታሰበው ጊዜ በፊት ቀድሞ መጠናቀቁም የዚሁ አንዱ ማረጋገጫ ነው፡፡ የዛሬው ድላችን በቀሪ የግንባታ ስራዎችም እንድንበረታ የሚያነሳሳን፤ በዲፕሎማሲ መስክም ይበልጥ ተደማጭ እንድንሆን ጉልበት የሚሰጠን አቢይ ስኬት እንጂ ላፍታም የምንዘናጋበት ሊሆን አይገባውም፡፡

ዛሬ የደረስንበት የግንባታ ደረጃና የውሃ ሙሊት የግድቡን ግንባታ ከጀመርን ወዲህ በመስኩ ከታዩ አንኳር ስኬቶች ተርታ የሚሰለፍ ቢሆንም ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር የምናደርገው ጉዞ በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደትናንቱ ለሀገራችሁ ብልፅግና ሁለንተናዊ ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በከፍተኛ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

በአባይ ወንዝ ላይ የሰራንው ግድብ ለእኛ የብልፅግናችን ሁነኛ መሰረት ሆኖ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እንድናቅድና እንድንፈፅም የሞራል ስንቅና የፋይናንስ ምንጭ የሚሆነን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ቢሆንም ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግሞ በመተባበርና በመከባበር ላይ ለተመሰረተ የጋራ እድገት መታሰቢያ እንዲሆን በሌለ አቅማችን ያበረከትነው ስጦታ ነው፡፡ ከህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ መጣል ጀምሮ የአባይ ውሃን የፍሰት አቅጣጫ ለመቀየር እንዲሁም አሁን የውሃውን ያልተገደበ የፍሰት ሁኔታ በፈለግነው መጠን ለመቆጣጠር መቻላችን በቅኝ ግዛት ውሎች ላይ የተመሰረተ አድሏዊ አሰራር የመሸበት፤ በአንፃሩ በጋራ ተጠቃሚነትና በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ ቀጠናዊ ትስስር ብሩህ ንጋት የፈነጠቀበት ሂደት ነው፡፡ የውሃ አሞላል ሂደታችን በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር መፈፀሙ በራሱ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በአንድነት የመበልፀግ አላማ እንጂ የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በተጨባጭ ያሳየ ነው፡፡

እኛ በላያችን ላይ የተጫነውን የድህነትና የኋላ ቀርነት ሸክም አሽቀንጥረን እስከምንጥል፡ የህዳሴ ግድባችን ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ሃይል ማመንጨት እስከሚጀምር ድረስ ለአፍታም አይናችን ከግድቡ ላይ አንነቅልም፡፡ የእስካሁኑ ስኬት ከኋላ እየተከተሉ ለሚጎትቱንና ከፊት እየቀደሙ ለማደናቀፍ የሚሞክሩ የውስጥና የውጪ ሃይሎች የክፋት ሴራቸው መቼም እንደማይሳካና የሀሰት ፕሮፖጋንዳቸው የከሸፈ መሆኑን የሚረዱበት እድል የሰጣቸው መሆኑን እናምናለን፡፡

ኢትዮጵያውያን “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!!” ብለን ከዘጠኝ አመት በፊት ቆርጠን የተነሳንበትን ይህን ብሄራዊ ፕሮጀክት በፈተናዎች ውጣ ውረድ ሳንበገር ይሄው ደግሞን “እንደጀመርነው ጨርሰንዋል!!” ብለን ለመዘመር ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ እንደ መሪ ፓርቲ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከታዩ ስህተቶች ተምረን፣ የህዝባችንን እምነት ሳናጓድል የግድቡን ግንባታ ከዳር እናደርሰዋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግታችሁ እንድትሰሩ፣ መላ የኢትዮጵያ ህዝቦችም ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ይህ ትውልድ የአያት ቅድመ አያቶቹን ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቹ የሚተላለፍ ህያው ታሪክ ሰርቶ ማለፍ እንደሚችል የህዳሴው ግድብ ህያው ምልክት ነው፡፡ ለአመታት የደከማችሁበት ግድብ ተጠናቆ ፍሬውን እስከምናይ መላ ኢትዮጵያውያን የመንግስት ተቋማትን መመሪያና የህክምና ባለሙያዎችን ምክር በመከተል ራሳችሁን ከኮሮኖ በሽታ እንድትጠብቁ ብልፅግና ፓርቲ አደራ ለማለት ይወዳል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት

ሐምሌ/2012 ዓ.ም

አዲስ አበባ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.