Fana: At a Speed of Life!

አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢዴፓ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
 
አቶ ልደቱ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
 
ፖሊስ በሰኔ 23 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት በቢሾፍቱ ለወጣቶች ገንዘብ በመስጠት ለብጥብጥ እና አመፅ በማነሳሳት በሚል ወንጀል እንደጠረጠራቸው አስታውቋል።
 
ባለፈው አርብ አራት ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው እና በዚህም ወቅት ሁለት ሽጉጦች ማግኘቱን አስታውቋል።
 
የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ለማቅረብም የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜንም የኦሮሚያ መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።
 
አቶ ልደቱ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቋሚ አድራሻ እና ቤት ያላቸው መታወቂያቸውም በዚያው መሆኑን በማንሳት በጊዜያዊነት በቢሾፍቱ ቤት እንዳላቸው በመግለፅ በፌደራል ፍርድ ቤት ነው መቅረብ ያለብኝ በሚል መቃወሚያ አንስተዋል።
 
በዋስ እንዲፈቱም በመጠየቅ የዛሬ ዓመት የልብ ቀዶ ጥገና ወዳደረጉበት ሀገር ዛሬ 4 ሰዓት ላይ ለመጓዝ የተዘጋጁ መሆናቸውን እና ትኬት ያላቸው ቢሆንም አሁን ታስረው እንደሚገኙ እና የአስም በሽተኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
 
የእስር አያያዙም ለኮቪድ-19 እንዳያጋልጠኝ ያሰጋኛል በማለት ይህ ታሳቢ ተደርጎ በዋስ ይፍታኝ ብለዋል።
 
መርማሪ ፖሊስ የእስር አያያዛቸው ምቹ እና ጥንቃቄ ያለው መሆኑን እና ከእስር ቢፈቱ ማስረጃ እንደሚሸሽበት በማሳወቅ ዋስትናውን ተቃውማል።
 
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው በዚያው በቢሾፍቱ አይታይ በሚል ላቀረቡት ወንጀሉ የተፈፀመው በቢሾፍቱ በመሆኑ እና መኖሪያቸውም በዚያው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እዚያው የማየት ስልጣን እንዳለው በማስረዳት ጉዳዩ በችሎቱ መታየት እንደሚቀጥል ትእዛዝ ሰጥቷል።
 
የዋስትና ጥያቄውንም ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
 
የአቶ ልደቱ ጠበቃም የክልሉ የጥብቅና ፍቃድ ባለማቅረባቸው ጥብቅና ሳይቆሙላቸው ቀርቷል።
 
ፍርድ ቤቱም ፍቃድ ከሌላቸው ማማከር እንደማይፈቀድላቸው ገልፆላቸዋል።
 
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.