Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባካሄዱት ውይይት ላይ የተነሱ ጉዳዮች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ጠዋት ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

ውይይቱ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከተካሄዱ የምክክር መድረኮች የቀጠለ መሆኑ እና የዛሬው ውይይት በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበረ ተጠቁሟል።

ውይይት የተካሄደባቸው ነጥቦችም

1 በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ እንዲካሄድ ቀጣይ አቅጣጫን ማስቀመጥ እና

2 የልማት ጉዳዮች እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን የመሳሰሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

የመጀመሪያውን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ፣ ተወያዮቹ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ውይይቶችን በፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ ለማስቀጠል ተስማምተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ቀጣዩ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ብሔራዊ መግባባት ይሆናል ነው የተባለው፡፡

ውይይቱም የሀገራችንን መልካም ተሞክሮዎች፣ እንዲሁም ብሔራዊ የታሪክ ምልከታዎች በቃኙ የጥናት ጽሑፎች ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ወቅታዊ ጉዳዮችን የተመለከተው ውይይት ላይ ከተነሱት ዓበይት አጀንዳዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
የታላቁ የሕዳሴ ግድብን የሥራ ክንውን መፋጠን በተመለከተ የፓርቲዎቹ አመራሮች ድጋፋቸውን ገልጸው፣ ከውጪ አካላት ጋር በመተባበር የሚደረጉ ጥረቶችን `ለማደናቀፍ የሚሰሩ የውስጥ ኃይሎችን ኮንነዋል።

የኮቪድ19ን ወረርሽኝ በተመለከተ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች እንዲሁም ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

ምርጫን በተመለከተ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በተናጠል እና ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ በክልል ደረጃ ምርጫን ለማካሄድ ጥረት ማድረጉ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓትን መናድ እንደሆነ ገልጸው፣ ሕገ-መንግሥቱን በመጻረር በሚደረጉ ተግባራት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሠራ ጠይቀዋል።

ነጻ እና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ በሚካሄድባቸው መንገዶችም ላይ ተጨማሪ ሃሳቦች ተነስተዋል።

ሰላም እና ደህንነትን በተመለከተ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፉ ገልጸው፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ጽንፈኞች እና ለውጡን የሚያደናቅፉ የቀድሞው ስርዓት ርዝራዦችን የማጥራት ሥራ እንዲሠራ ጠይቀዋል።

መንግሥት በሕገ-መንግሥቱ የተሰጠውን ሕግ የማስከበር ሥልጣን በሚገባ እንዲጠቀም፣ ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያውኩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ሀሳቦች ተነስተዋል።

ተቋማዊ ግንባታን በተመለከተም ሕግ የማስከበር ሂደትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በሕግ ማስከበር ስርዓት፣ በፍትሕ ስርዓት እና ተቋማዊ መዋቅሮች ውስጥ ባለፈው የተተገበሩ እና ፍትሐዊ ያልሆኑ ተግባራትን ለማረም እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቀዋል።

በምላሹም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለ ሰላማዊ ተሳትፎ ጠቃሚነት፣ በግልጽ ሀሳቦችን አቅርቦ መወያየት ስላለው ዋጋ እና በፖለቲካዊ ምክክሮች ወቅት እርስ በእርስ ስለ መከባበር አስፈላጊነት አንስተዋል።
“ጥንካሬ የሚገለጸው ገንቢ ሃሳቦችን በማፍለቅ እንጂ በጡንቻ አማካኝነት አይደለም” በማለት አበክረው ተናግረዋል።

ተቋማዊ ግንባታን አስመልክቶም፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አውዳሚ ግለሰቦች እና ሌቦች መኖራቸውን እና ለውጡን ለማደናቀፍ እንደሚተጉም አንስተው፣ የተቋማት ግንባታ ረዥም ጊዜን የሚፈጅ እና በቀላሉ ሊታይ የማይገባው ሂደት እንደሆነ ተናግረዋል።

ውስጣዊ ማጥራትን የማካሄድ ሥራው እንደሚቀጥል እና ቀስ በቀስ ተቋማዊ ማነቆዎች እንደሚወገዱም አሳውቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም እሰካሁን የተከናወኑትን ወሳኝ ምዕራፎች እንዳይዘነጉ አሳስበዋል።

ሰላም እና ደህንነትን አስመልክቶም፣የጥፋት አቀናባሪዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው ሊነኩ እንደማይገባ መታሰቡ ስህተት እንደ ሆነ ተናግረዋል።

ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች መጫወት ያለባቸው በተምሳሌታዊው ሜዳ ውስጥ ሆነው እንጂ፣ ፖለቲካዊ ፉክክሮችን ለማስተናበር በተቋቋሙ ተቋማት ላይ በመነሳት እና ከሕግ ውጪ በመሆን አይደለም።

የተካሄዱት እስሮችም በቅርቡ በተፈጸመው የአመጽ ሥራ ውስጥ የተሳተፉ ወይም መወጣት ያለባቸውን ኃላፊነት ያልተወጡ የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ጭምር ማካተታቸውን አስታውሰው፣ ቀለል ተደርጎ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎችን ዒላማ እንዳደረገ መታሰብ እንደሌለበት ተናግረዋል።

ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው አካላት መጠየቃቸውም ይቀጥላልም ነው ያሉት።

“ማንም ሰው ጤናው እንዲጓደል አንሻም፣ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ሁኔታዎችን እናስተካክላለን። ነገር ግን፣ ሕግ የበላይ ሆኖ ይቀጥላልም ብለዋል።

በቅን ልብ በእስር ላይ ያሉ ግለሰቦች እንዲፈቱ ለማሸማገል በግል የሚቀርቡኝን ሰዎች ቅንነት ባከብርም፣ ጥያቄያቸው የፍትሕ ስርዓቱ እንዲዛባ የሚያደርግ በመሆኑ እና እኔ በግሌ የሚፈታንም ሆነ የሚታሰርን ሰው ለመምረጥም ለመወሰንም የማልችል በመሆኑ አግባብነት የለውም” በማለት ተናግረዋል።

በመጨረሻም፣ ኢ-ሕገመንግሥታዊ የሆኑ የክልል ምርጫዎችን አስመልክቶ፣ ፌደራል መንግሥት ግጭት ቆስቋሽ በሆኑ ክልላዊ መንግሥታት ላይ ኃይልን መጠቀም እንደማይፈለግ አስገንዝበዋል፡፡

የፌደራል መንግሥት የኃይል እርምጃን እንደሚወስድ በማሰብ በግልጽ ግፊት እየተደረገበት ቢሆንም፣ ሀገሪቱን የሚያስተዳድሩ ተቋማት እና ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ ተጠናክረው መከናወናቸውን ይቀጥላሉ ሲሉ ተናገረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በተቋቋመው ጥምር ኮሚቴ አማካኝነት ሲካሄዱ ከቆዩት የፓርቲ ለፓርቲ ውይይቶች ባሻገር፣ የፌደራል መንግሥት ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.