Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ በተፈፀመ ጥቃት የ13 ዜጎች ሕይወት ማለፉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ በተፈፀመ ጥቃት የ13 ዜጎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ከሀገር ውጭና ከውስጥ ተልዕኮ የተሰጣቸው የጥፋት ኃይሎች ሐምሌ 20 ቀን 2012 ምሽት አካባቢ አቡጃር ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት የ13 ንጹኃን ዜጎች ሕይወት አልፏል ብለዋል፡፡

የጥፋት ቡድኑ ተገቢ ስልጠናና ተልዕኮ በመያዝና በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት የማስተጓጎል እና የብሔር ግጭት የመቀስቀስ ዓላማ በመያዝ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱንም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ቀደም ብሎ በአካባቢው ሠላምን ለማረጋገጥ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱንም አስታውቀዋል፡፡

በጥፋት ቡድኑ ላይ እየተወሰደ ካለው እርምጃ በተጨማሪ አራቱ በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉት አቶ አብዱላዚዝ÷ እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የአካባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ አሁንም የተጠናከረ ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን በመጠቆም፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በስፍራው ተገኝተው ህብረተሰቡን በማረጋጋት ላይ እንደሆኑ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የክልሉ መንግስት በንጹኃን ዜጎች ላይ በደረሰው ጥቃት ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው በመግለጽ፣ ድርጊቱ የሚወገዝ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ የአማራ ክልል መንግስት በጥቃቱ በንጹኃን ዜጎች በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሀዘን መግለፁ የሚታወስ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.