Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በነገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እየጠበቀ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በነገው ዕለት በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እየጠበቀ እንዲሳተፍ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ዑማ ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ከንቲባው በነገው ዕለት በሚተከለው 2 ሚሊየን ችግኝ ዙሪያ ለከተማው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የከተማዋ ነዋሪዎች በመዲናዋ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴርና ከከተማዋ ጤና ቢሮ እየተሰጡ ያሉ መመሪያዎችን በአግባቡ እንዲተገብሩ አሳስበዋል።

በከተማዋ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሊተከል በእቅድ ከተያዘው 7 ሚሊየን ችግኝ መካከል ከ4 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የሚሆነው ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎችን በማሳተፍ መተከሉን አንስተዋል።

የጋራ ቤታችን የሆነችውን አዲስ አበባን በጋራ እንገንባ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች በመኖራቸው ለከተማ ግብርና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉም ነው ያሉት፡፡

ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ የችግኝ መትከል ጥቅሙን ከወዲሁ የሚያመላክት ነው ብለውታል።

በመሆኑም በነገው ዕለት የከተማዋ ነዋሪዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው እና ለተከላ በተዘጋጁ ስፍራዎች ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ በነገው ዕለት ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የ2 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ይከናወናል።

በምስክር ስናፍቅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.