Fana: At a Speed of Life!

አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት መምህራንና ተመራማሪዎች የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 25 ፡ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት መምህራንና ተመራማሪዎች የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ።

ዩኒቨርሲቲው በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጠው ለፕሮፌሰር አሰፋ አባሙና እና ለፕሮፌሰር አማን ደቀቦ ነው።

አሁን ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ምሁራን በረጅም ጊዜ ማስተማር፣ ጥናትና ምርምሮቻቸውን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች በማሳተምና በማህበረሰብ አገልግሎት አበርክቶዎቻቸው ማዕረጉ እንደተሰጣቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ተናግረዋል።

አክለውም ማዕረግ መሰጠቱ የምሁራንን ተወዳዳሪነት ይጨምራል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ጊዜ ከ400 በላይ የዶክትሬት ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ሲሆን ትምህርቱን በጥራት ለመስጠት ምሁራንን የማብቃት ስራ እየሰራ ነው ተብሏል።

በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሹመቴ ግዛው ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በሌሎች ስራዎች ሊገለጥ ይገባል ብለዋል።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲው የተጀመሩ የሽግግር ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሰው ሀይል ማብቃቱን ማጠናከር እንደሚገባውም አውስተዋል።

ማዕረጉ የተሰጣቸው ምሀራን በበኩላቸው የበለጠ ለመስራት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.