Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ቀጥሎ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በትናንትናው እለት ቀጥሎ መካሄድ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት የሶስትዮሽ ድርድሩ በቪዲዮ ኮንፍረንስ መካሄድ መጀመሩንም ነው የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።

የአፍሪካ ህብረት በሚመራው ድርድሩ ላይም ታዛቢዎች እና የአፍሪካ ህብረት የመረጣቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸውም ተገልጿል።

በሶስትዮሽ ድርድሩ ላይም የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ፍትሓዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ እንዲሁም ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ድርድሩን ለመቋጨት ትሰራለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ መሪዎች ባስቀመጠጡት አቅጣጫ መሰረትም በግድቡ የውሃ ሙሌት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ አጠቃላይ ስመምነት ላይ መድረስ እንደሚገባም ገልፀዋል።

የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር አካሄድ ላይ ከስምምነት የደረሱ ሲሆን፥ ድርድሩም ለቀጣይ ሁለት ሳምንታት ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል።

በሁለት ሳምንታት የድርደር ሂደቱም ከሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ በተጓዳኝ  የዘርፉ ባለሙያዎች ስብሰባዎች እንዲሁም ከታዛቢዎች እና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ምክክሮች እንደሚደረጉም ነው የተመላከተው።

በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለ11 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ባሳለፍነው ሐምሌ 6 2012 ዓ.ም መቋረጡ ይታወሳል።

ድርድሩ ተቋርጦ የቆየውም በሱዳን በኩል በቀረበው የይዘግይልኝ ጥያቄ መሠረት ሲሆን፥ ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ መካሄድ ጀምሯል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.