Fana: At a Speed of Life!

ከሌላ ሀገራት ወደ ቻይና ከገቡ የታሸጉ የምግብ ምርቶች የኮሮና ቫይረስ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሁለት የቻይና ከተሞች በካርጎ ወደ ቻይና ከገቡ የታሸጉ የምግብ ምርቶች የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።

ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት በታሸጉ ምግቦች በኩል የኮሮና ቫይረስ ወደ ሰዎች የመተላለፍ እድል እንደሌለው ገልጿል።

ከብራዚል ወደ ቻይናዋ ደቡባዊ ከተማ ሼንዝሄን ከገባ የታሸገ የዶሮ ስጋ ከክንፍ የውጨኛው ክፍል በተወሰደ ናሙና የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ ከኢኳደር ወደ ሰሜን ምዕራብዊቷ ሺያን ከተማ ከገባ ስጋ ነክ ምርት ማሸጊያ በተወሰደ ናሙና ቫይረሱ መገኘቱን የአካባቢው ባለስልጣናት መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

የሼንዝሄን ባለስልጣናት የታሸገውን ዶሮ ምርት ያዘጋጀው ብራዚል የሚገኘው አሮራ የተባለው ግዙፍ የዶሮ እና አሳማ ምርቶች ላኪ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎም የኮሮና ቫይረስ በምግብ ምርቶች የውጨኛው ክፍል ተስፋፍቶ ወደ ምግብ ሰንሰለቱ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ እየተነሳ ይገኛል።

ከ100 ቀናት በኋላ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባት ኒውዝላንድም ቫይረሱ ወደ ሀገሯ በየብስ፣ በባቡር እና በአየር የጭነት አገልግሎት ምክንያት ገብቶ ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ ምርመራ መጀመሯን አስታውቃለች።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ሰዎች ከምግብ ጋር ተያይዞ የኮሮና ቫይረስ ሊይዘን ይችላል ብለው ሊፈሩ አይገባም ብሏል።

የአሜሪካ ምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር እና የግብርና ክፍል በጋራ ባወጡት መግለጫ ሰዎች ከምግብ ነክ ምርቶች የኮሮና ቫይረስ እንደተላለፈባቸው የሚያረጋግጥ መረጃ የለም ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.