Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ የክረምት ወራት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀጣዮቹ የክረምት ወራት ነሀሴና መስከረም መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በዚህም የሰሜን ምዕራብና የምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸው ኤጀንሲ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

አብዛኛው የደቡብ ምዕራብ፣ የመካከለኛው፣ የምስራቅና የደቡብ ደጋማ እንዲሁም የሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎችም ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡

ኤጀንሲው ከሚጠበቀው ከፍተኛ እርጥበት ጋር ተያይዞ በሰብሎች ማሳ ላይ የውሀ መተኛት ሊከሰት ስለሚችል የዘርፉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ቦይ በማውጣትና የውሀ ማጠንፈፍ ስራ በማካሄድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ከሚፈጠረው ነጎድጓድ አዘልና በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የወንዞች ከመጠን በላይ መሙላት እንዲሁም ቅጽበታዊ ጎርፍ በረባዳማ ቦታዎችና ጎርፍ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ ሊከሰት ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡

የክረምት ዝናብ አወጣጥን በተመለከተም መደበኛ የዝናብ አወጣጥ የሚኖር መሆኑን የጠቆመው ኤጀንሲው በመጭው የበጋ ወቅትም የዝናብ ማነስ የሚያጋጥም በመሆኑ አርብቶ አደሩ እና ከፊል አርብቶ አደሩ ቀሪ የክረምት ወራቶቹን በከፍተኛ ሁኔታ ውሀ ለማቆር ሊጠቀምባቸው ይገባል ነው ያለው፡፡

በትዝታ ደሳለኝ

ፎቶ÷ ከማህበራዊ ሚዲያ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.