Fana: At a Speed of Life!

ለማህበራዊ ችግሮች ዕልባት በመስጠት በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ዜጎች የስራ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው-የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስር ለሰደዱ ማህበራዊ ችግሮች ዕልባት በመስጠት በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ዜጎች የስራ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የቀጣዮቹን አስር አመታት ዕቅድ መነሻ ያደረገ ውይይት ከተጠሪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ይገኛል፡፡

በመድረኩ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ኮቪድ-19 የሚያደርሰውን ጫና መቋቋም የሚችል የሰራተኛና ማህበራዊ ዘርፍ ልማት ለማረጋገጥም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ኮቪድ-19 በዘርፉ ሊፈጥር የሚችለውን ቀውስ ለመቀነስ ተግባራዊ የተደረገው የስራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮል ተቋማትና ድርጅቶች ከሰራተኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ዙሪያ መመሪያ በማውጣት በርካታ ዜጎችን እንደታደገም ተገልጿል፡፡

21ሺህ 380 ድርጅቶችም በፕሮቶኮሉ አተገባበር ዙሪያ የግንዛቤ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡

በበጀት አመቱ እስከ 50 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የውጭ ሃገራት የስራ ስምሪትን ለመስጠት ታቅዶ ኮቪድ-19 እስከተከሰተበት ወቅት ለ16 ሺህ ሰራተኞች የውጭ ሃገራት የስራ ስምሪቱን መስጠት መቻሉ ነው የተመላከተው፡፡

ሃገራት በወረርሽኙ ሳቢያ ድንበራቸውን ዝግ በማድረጋቸው ምክንያት ዕቅዱን ከ33 በመቶ በላይ ማድረስ እንዳልተቻለም በመድረኩ ተነስቷል፡፡

በሌላ በኩል ከኮቪድ-19 በፊት ከ15 ሺህ በላይ ለሆኑ ከስደት ተመላሽ ዜጎች የመልሶ ማቋቋም ስራ መከናወኑም የተገለፀ ሲሆን በዚሁ ወረርሽኝ የተነሳ እስከ ሰኔ 30 ብቻ ከ19 ሺህ በላይ ሰራተኞች ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል ተብሏል፡፡

ድንገተኛ የነበረውን የኮቪድ-19 ክስተትና ተመላሾችን በመመርመር ወደመጡበት ክልል እንዲመለሱ በማድረግ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሩ አፈጻጸም ነበረው ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም በቤሩትና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በችግር ላይ መሆናቸውና ባሉበት የስራ መብታቸውን ከማስጠበቅም ሆነ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ከማድረግ አኳያ ፈጣን ዕልባት እንደሚሹም በውይይቱ ተነስቷል፡፡

የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከልም ከኳታር መንግሥት ጋር በመተባበር 8 ነጥብ 5 ቶን የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስን ወደ ሃገሪቱ ማስገባቱ ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከመቀነስ፣ አረጋውያንንና አካል ጉዳተኞችን ከመደገፍ አንጻርም የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ነበሩ ያለው መስሪያ ቤቱ፤የኮቪድ-19 ተፅዕኖንም ሆነ ነባር የዘርፉ ችግሮችን የበለጠ ለማቃለል ማህበራት፣ ባለሃብቶችና መንግሥት በህብረት እንዲሰሩ ጠይቋል፡፡

በሶዶ ለማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.