Fana: At a Speed of Life!

በ2012 በጀት ዓመት ከ15 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት 15 ሺህ 192 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻሉን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በፅህፈት ቤቱ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ቴክኒካል ድጋፍ እና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰናይ ገብረጊዮርጊስ እንዳስታወቁት፣ በበጀት ዓመቱ 16 ሺህ 165 ነጥብ 48 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዕቅድ ተይዞ 15 ሺህ 192 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል፡፡

አፈፃፀሙም ከእቅዱ የ6 ነጥብ 2 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በበጀት ዓመቱ የተጠበቀውን ያህል የኃይል ጥያቄ አለመቅረቡ እና የደንበኞች የሌሊት የኃይል አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ ለእቅዱ አለመሳካት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡

የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ወደ ኦፕሬሽን አለመግባቱ፣ የገናሌ ዳዋ 3ኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በታቀደው ጊዜ ኃይል ማመንጨት አለመቻሉ እና ለጣቢያዎች የመለዋወጫ ዕቃ ባለመሟላቱ በጥገና ችግር የቆሙ የማመንጫ ዩኒቶች መኖራቸው ለእቅዱ አለመሳካት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሃገሪቱ የኃይል እጥረት አለመከሰቱንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማመንጨት የተቻለው ኃይል ከ2011 በጀት ዓመት አመት ጋር ሲነጻፃፀር የ9 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ መኖሩንም ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ 21 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ጣና በለስ፣ ግልገል ጊቤ I፣ ጊቤ II፣ መልካ ዋከና፣ ጢስ ዓባይ II፣ ቆቃ፣ አዋሽ 2፣ አመርቲ ነሼ እና ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ጣቢያ ከታቀደላቸው በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻላቸውም ተጠቁሟል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ደንበኞች አገልግሎት የሚውል 17 ሺህ 307 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት እቅድ መያዙን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.