Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ፣ የአማራ ክልሎችና ገቢዎች ሚኒስቴር በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ፣ የአማራ ክልሎችና ገቢዎች ሚኒስቴር በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረጉ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው እና የኦሮሚያ ክልል ልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት ድጋፉን አስረክበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ካለው የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት ለአፋር አርብቶ አደሮች እንዲውል 900 ኩንታል እህል ለክልሉ መንግሥት ማበርከቱን ተነግሯል።

ከዚህ ውስጥ 100 ኩንታሉ ለነፍሰጡር እናቶችና ሕፃናት የሚውል አልሚ ምግብ ይገኝበታል።

በቀጣይም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የኦሮሚያ ክልል ልዑካን ቡድን አባል አቶ ንብረቱ ታረቀኝ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል 500 ብርድ ልብስ፣ 500 ጥንድ አንሶላዎች፣ 500 ፍራሽና 1 ሺህ 500 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን ያበረከቱት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ሁላችንም የሉሲ ልጆች በመሆናችን የአፋር ሕዝብን መደገፍ የራሳችንን ሕዝብ እንደመደገፍ ነው ብለዋል።

አቶ ተመስገን በቀጣይም በጎርፍ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እስኪመለሱ ድጋፉ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ የገቢዎች ሚኒስቴር በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ደግሞ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ፣ ዱቄትና ፓስታ ድጋፍ ማድረጉን ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያለው ተናገረዋል።

አቶ ላቀ አያሌው በክልሉ በጎርፉ አደጋ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ መሥሪያ ቤታቸው ከአፋር ክልል ከጎን መሆኑን ለማሳየት መምጣታቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ሚኒስቴሩ በተለያዩ ጊዜያት በክልሎች ተከስተው በነበሩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.