Fana: At a Speed of Life!

ተቀጣጣይ ፈንጆች ፣ አሞኒየም ናይትሬትና ሌሎች የኬሚካል ክምችቶች በአጠቃቀምና በአያያዝ ጉድለት ጉዳት እንዳያስከትሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈንጂ ለልማት አውታሮች ግንባታም ሆነ ለማዕድን ቁፋሮ ያለውን ጠቀሜታ ያህል በአያያዝና በአጠቃቀም ጉድለት ምክንያት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ጉዳት አኳያ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ሊሆን እንደሚችል የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ከ120 በላይ የሲቪል ኢንዱስትሪያል ፈንጅና ተቀጽላ ተጠቃሚዎች ጋር ውይይት አካሂዷል። መድረክ ላይ ነው፡፡
 
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ፈንጂን ለልማት አውታሮች እንዲሁም ለማዕድን ቁፋሮና መሰል የኮንስትራክሽን ግንባታዎች ለሚያውል አካላትና ድርጅቶች ፈቃድ ከመስጠት በተጨማሪም ለታለመለት አላማ መዋሉን የመቆጣጠር፤ የመከታተልና ሙያዊ ድጋፍ የመስጠት ህጋዊ ስልጣን ተሰጥቷል፡፡
 
አገልግሎት መስሪያ ቤቱ እስከአሁንም ለ252 ለአገር በቀልና ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ገብተው መዕዋለ ንዋያቸውን እየፈሰሱ ላሉ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ፈቃድ መሰጥቱን አስታውቋል።፡፡
 
ተቀጣጣይ ፈንጆች፤አሞኒየም ናይትሬትና ሌሎች የኬሚካል ክምችቶች በአጠቃቀምና በአያያዝ ጉድለት እንዲሁም በቸልተኝነት ምክንያት በሰሜን ኮሪያ፤ በቻይና በቅርቡ ደግሞ በሊባኖስ ቤይሩትና በሌሎችም አገራት ላይ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት መነሻ በማድረግ ስጋቱን አስቀድሞ ለመከላከል በአገራችንም ፈቃዱን ወሰደው ከሚንቀሳቀሱ አካላትና ድርጅቶች ጋር ከአጠቃቀም አያያዝና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
 
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ ፈቃዱን ወሰደው በሚንቀሳቀሱ አካላትና ድርጅቶች ላይ ባደረገው የኦዲትና የኢንስፔክሽን ስራዎች ከትራንስፖርት ፣ ከፍንዳታ ፣ ከአያያዝ ፣ ከግዢ ፣ ከሽያጭና ከሌሎች ተጓዳኝ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ ጉድለቶችና ክፍተቶች ማግኘቱን በመድረኩ ላይ አስታውቋል፡፡
 
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ችግር የታየባቸውን የአራት ድርጅቶች ፈቃድ መሰረዙን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመልክቷል።
 
በዉይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ ከ120 በላይ ፈንጂና ተቀጽላ ተጣቃሚ አካላትና ድርጀቶችም ከትራንስፖርት ፣ ከአያያዝና ከአጠቃቀም ጋር በተያያዘ በአንድ አንድ አካላትና ድርጅቶች ላይ ቸልተኝነት መኖሩን አምነው በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
 
የጉዳዩን አሳሳቢነትና ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ፈቃድ በወሰዱ አካላትና ድርጅቶች ላይ የሚያደርገውን ጥብቅ የኦዲትና የኢንስፔክሽን ስራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል በአዋጅ የተሰጠውን ስልጠና መሰረት በማድረግ አሰራሮችን ለማዘመን መመሪያዎችን የመከለስ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
 
ክፍተቶችን ለማረም የሙያና የክህሎት ስልጠናዎችን ለፈንጅ ተጠቃሚዎች መስጠት እንደሚቀጥልና የጉዳዩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት በመምሪያው መሰረት በማይሰሩ አካላትና ድርጅቶች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
 
የፈንጅና ተቀጽላ ተጠቃሚ አካላትና ድርጅቶች ማከማቻወዎቻቸውን ከከተማ ውጭ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዘኖችን በመገንባት እንዲያዘዋውሩ ፣ የጥበቃ ስርዓታቸውንም እንዲያጠናክሩ እንዲሁም የፍንጅ ፍንዳት ሲያካሂዱም ተቋሙ ያስቀመጠውን መመሪያ ተከትለው በሰዎችና በንብረት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጭምር አገልግሎት መስሪያ ቤቱ አሳስቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.