Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት አቅጣጫዎችን አስቀመጠ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ በወቅታዊ ሀገራዊ እና የፓርቲ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡

በፓርቲው ውይይት ተደርጎባቸው የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎችና የተቀመጡ የወደፊት አቅጣጫዎችን በሚመለከት መግለጫ ያወጣ ሲሆን የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 

ፈተናን ወደ ጥንካሬ እየቀየርን የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን እናደርጋለን!

ከብልጽግና ፓርቲ ራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

 

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ነሐሴ 11/2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በወቅታዊ ሀገራዊ እና የፓርቲ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡ በፓርቲው ውይይት ተደርጎባቸው የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎችና የተቀመጡ የወደፊት አቅጣጫዎችን በሚመለከት ተከታዩን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የተወደዳችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

ሀገራዊ ለውጡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ድልን፣ ፈተናን እና ተስፋን እያፈራረቀ በዓይነቱና በፍጥነቱ ወደተለየ አዲስ ምእራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡

ያለፈው ሁለት ዓመት ከጭቆና እና አምባገነን ስርዓት ወጥተን የዴሞክራሲ ሥርዓት በማስፈን ረገድ ተስፋ የፈነጠቀበት ጊዜ ነው፡፡ በብልሹ አሠራር ምክንያት የተጓተቱ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በነቃ የአመራር ክትትል ወደ መጠናቀቅ ምእራፍ ተሸጋግረዋል፡፡ ከኢኮኖሚ መፋዘዝ መነቃቃት ወደታየበት የእድገት ምእራፍ ገብተናል፡፡ በጥርጣሬና በአሸናፊና ተሸናፊ ዕሳቤ ላይ ከተመሠረተ የጎረቤት ሀገራት ግንኙነት ወጥተን መተማመንና የጋራ ተጠቃሚነትን እንዲሁም የዜጎች ክብርን ያስቀደመ የውጭ ግንኙነት የተተካበት ወቅት ነው፡፡ ከመራራቅ የጥላቻ ትርክት ወጥተን በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል የወንድማማችነት ትርክት ላይ የተመሠረተ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የጀመርንበት ፈጣንና ጥልቅ የለውጥ ምሕዋር ጊዜ ነው ያለፈው ሁለት አመት፡፡

ሀገራዊ ለውጡ የፈነጠቀው ተስፋና ድል እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በበርካታ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችና ፈተናዎች ውስጥ ስትፈተን ቆይታለች፡፡ በዕድገታችን የሚከሥሩ፣ በውድቀታችን የሚያተርፉ አካላት የዘመናት የሕዝቦች ጥያቄና ፍላጎት የሆነውን ዴሞክራሲን የመትከልና የማጽናት ትግልን ለመቀልበስ ሲጥሩ ቆይተዋል፤ አሁንም እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ከንቱ ዓላማቸው ስኬት ሀገርን በማተራመስ ግላዊ የሥልጣን ፍላጎታቸውን ለማርካት እየደከሙ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ለለውጥ እንዳይተጋና በለዉጡ ተስፋ እንዲቆርጥ በመፈለግ የተቀናጁ ቡድኖች ሕዝብን ለሞት፣ ንብረትን ለውድመት ዳርገዋል፡፡ የእነዚህ ቡድኖች የጥፋት ተልዕኮ ለውጡን ከመቀልበስም ባሻገር ሀገርን የማፍረስ ግብ እንዳለው ከድርጊታቸው የተረዳንው ነው፡፡ ነገር ግን የተረጋጋ እና በሳል አመራር ለመስጠት በመቻላችን እንዳሰቡት ለውጡን ለመቀልበስና የተለወጠውን “አሮጌ ሥሪት በአዲስ አቁማዳ” ለማስቀጠልም ሆነ ሀገር ለማፍረስ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ከሰው ሠራሽ ፈተናዎች ባሻገር የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ የቀየረው የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ እና የጎርፍ ተፈጥሯዊ አደጋዎች የደቀኑብን ፈተና ሀገራዊ ለውጡ ውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል፡፡ ፈተናን ወደ ጥንካሬ፣ ተግዳሮትን ወደ መልካም ዕድል የሚያሸጋግር ዝግጁነትና ፈጣን ምላሽ የሰጠ አመራር በመፈጠሩ የኮሮና ወረሽኝ በሕዝባችን ጤና እና ኢኮኖሚ ላይ ሊያሳርፍ ይችል የነበረውን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ መቀነስ ተችሏል፡፡ በዚህ አኩሪ ሥራም ፓርቲያችንና መንግሥት ሕዝቡን ከጎናቸው በማሰለፍ ሀገርንና ሕዝብን የማዳን አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡

የኮሮና ወረሽን በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመከላከል 10 ቢሊዮን ብር ለግሉ ዘርፍ ፈሰስ ተደርጓል፡፡ ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። የውጭ ንግድ ዘርፉ ላለፉት አራት ዓመታት ይጓዝበት የነበረውን የቁልቁለት ጉዞ እንዲገታ በማድረግ የውጭ ንግዳችን በ2012 የበጀት ዓመት አምና ከነበረው የ14 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ከ3 ቢልዮን ዶላር በላይ አስገኝቷል።

የኮሮና ወረርሽኝ በግብርና ዘርፍ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እና የምግብ እጥረት እንዳይገጥመን ለማድረግ በመኸር ወቅት ‹‹አንድም ማሳ ጾም ማደር የለበትም›› በሚል መርሕ ተንቀሳቅሰናል፡፡ በዚህ መርሐችን በአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ በኩታ ገጠምና በመሥመር መዝራትን ጨምሮ 11.7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ተችሏል፡፡ የበረሐ አንበጣ ወረራን ለመከላከል ክሥተቱ ከታየበት አጠቃላይ መሬት ውስጥ 95 በመቶ በሚሆነው ላይ የኬሚካል ርጭት በማድረግ ችግሩን ለመግታትና ወረራው እንዳይስፋፋ ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡

የተከበራችሁ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፤

ፓርቲያችንና መንግሥት የገጠሟቸውን ፈተናዎች ወደ ውጤት የመቀየር ዐቅም እና የተጀመረውን የመጨረስ ብርታት እንዳላቸው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡ ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ እና ተስፋ ያረፈበትን ግድብ ከገባበት የፕሮጀክት አፈጻጸም ቅርቃር መንጥቀን በማውጣት በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ወደ ሥራ ለመግባት በመቻላችን ዛሬ ላይ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውኃ ሙሌት አካሂዷል፡፡ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸምም በመገባደድ ላይ ይገኛል፡፡ የሕዳሴ ግድብን አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ከውስጥ ባንዳዎች እስከ ውጭ ጠላቶች’ ብዙ ተዘምቶ ነበር፡፡ ዓላማችን ለሀገራችን አሻራ ማኖር በመሆኑ ጊዜያዊ አቧራ ዓይናችንን ሳይከልለን፣ የደረሰብንን የዲፕሎማሲ ፈተናዎች በጥበብ በማለፍ፣ የሀገራችንን ዘላቂ ጥቅም ሳናስነካ እና ጎረቤቶቻችንን ሳንጎዳ፣ ለጋራ ተጠቃሚነት ያለን የማይናወጥ ዐቋም ለዓለም አሳይተናል፡፡ የሕዳሴ ግድብ የሀገራችን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በተባበረ ክንድ ‘ከዕለት ጉርሱ፤ ከመት ልብሱ’ ቀንሶ ታሪካዊ አሻራውን ያኖረበት፤ ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ድንቅ ታሪክ መሥራት እንደምንችል ያሳየንበት ዳግማዊ የዐድዋ ድል ነው፡፡

ውድ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ዝቦች

ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ትልም የሚሳካው በሕዝቦች ትሥሥርና ወንድማማችነት እንደሆነ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡ ጤናማ ማኅበረሰባዊ ትሥሥር የሚፈጠረው ከራስ ተሻግሮ ለማኅበረሰብ በሚደረግ ግልጋሎት እንደሆነ በሚገነዘቡ ከ10 ሚልዮን በላይ በሚሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ወጣቶች የደካሞች ቤት ታድሷል፤ ማዕድ ማጋራት ተችሏል፣ እንዲሁም የኮሮናን ወረርሽኝ ለመቋቋም የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ግልጋሎቶች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ተደርገዋል፡፡ በጎ ፍቃደኝነት የአንድ ወቅት ተግባር ብቻ ሳይሆን የወጣቱ የሁልጊዜም የሕይወት እንቅስቃሴና ልማድ አካል እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት የመግባባት፣ የወንድማማችነት፣ የሀገር ባለቤትነት፣ የእርስ በእርስ መተማመን እና ትሥሥር ነጸብራቅ በመሆን የጥላቻን ግንብ ደርምሶ ሀገር የሚገነባበትን ድልድይ የሚሠራ እንዲሆን የማድረግ ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በጎ ፈቃደኞች ከሚያውቁት አካባቢና ክልል ወጥተው በሌሎች ክልሎች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና አካባቢዎች አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ ለሕዝብ ትውውቅን፣ ትብብርንና አንድነትን እንዲያጎለብቱ መደረግ አለበት፡፡

ድህነትን፣ የመሬት መራቆትን፣ የበረሃማነት መስፋፋትን በመግታት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ አረንጓዴ መሆን ይገባታል ብሎ ፓርቲያችን  በጽኑ ያምናል፡፡ አረንጓዴ አሻራ በገንዘብ የማይተካ የተፈጥሮ ሀብትን የሚጠብቅ፤ ዘላቂና የጋራ ብልጽግናን የሚያረጋገጥ ነው፡፡ በዘንድሮው ክረምት “ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን እየጠበቅን አካባቢያችንን እናለማለን” በሚል መርሕ የተመራው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር፣ 5 ቢልዮን ችግኞችን በመትከል በዓለማችን በዓመት ከሚጠፋው የደን ሽፋን ሲሦውን በሀገራችን በመተካት በድል ተጠናቋል፡፡ አምናን ጨምሮ በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የሀገራችንን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ነው፡፡ በቀጣይ ይህንን ተሞክሯችንን በማስፋት በመደመር ዕሳቤ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በመተባበር፣ አረንጓዴ አሻራችንን በቀጠናው በጋራ ለማኖር የምንሠራ ይሆናል፡፡

የተከበራችሁ የፓርቲያችን አባላትና አመራሮች

ያሳለፍናቸው ሁለት የለውጥ ዓመታት፣ ለውጡ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ለማለፍ እንዲችል፣ በአንድ በኩል የፀረ ለውጥ ኃይሉን ተሸናፊነት የማይቀይሩ እኩይ ድርጊቶችን መመከት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአመራሩን የአስተሳሰብና የተግባር መዛነፍ ማረቅ ተገቢ መሆኑን በተጨባጭ አሳይተውናል፡፡ በለውጡ ማግሥት ያስመዘገብናቸው ድሎች በአመራራችን አብሮነትና ትጋት የመጡትን ያክል በለውጡ ውስጥ እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች በአመራር ድክመትና ውድቀት ከመንገዳችን ሊያደናቅፉን እንደሚችሉ እማኞች ናቸው፡፡ በመሆኑም የፓርቲያችን አባላትና አመራሮች ለሕዝባችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች በመሥራት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የተቃና ለማድረግ የሚችል ዝግጁነት ዐቅምና ቆራጥነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ታሪክ አስተምሮናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለሕዝቦች ወንድማማችነትና ትብብር ቀናዒ የሆኑ፣ ከፍተኛ የማስፈጸም ብቃት ያላቸው እና ከሌብነት የጸዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ባሳለፍነው የለውጥ ሂደት ምንም እንኳን አብዛኛው አመራራችን ተልእኮውን ጠንቅቆ በመረዳት ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በማሳየት በቁርጠኝነት ቢሠራም፤ በጎራ መደበላለቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡና ከጥፋት ኃይሎች ጋር የተባበሩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን በማጥራት ፓርቲያችን ጥንካሬውን ይዞ እንዲቀጥል ርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል፡፡ በቀጣይም ተከታታይ የሆነ የግንባታ እና የአመራር ማጥራት ሥራ በመሥራት አመራሩ ሀገራችንን ወደምታልመው ሁለንተናዊ ብልጽግና ማድረስ የሚያስችል ዐቋምና ቁመና ላይ እንዲደርስ የሚያበቃ ሥራ በቁርጠኝነት እንሠራለን፡፡

የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን የማስፋቱ ሥራ ወደ ኋላ እንዳይመለስ፣ የሕዝቦች ወንድማማችነት እንዲጠናከር፣ የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና የኮሮና ወረሽኝ ለመከላከልና ለመቋቋም የተጀመረው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ሕዝባችንን በማሳተፍ ግለቱን ጠብቆ እንዲፈጸም የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም የዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በሰላም የመኖር፣ የመሥራትና የመንቀሳቀስ መብት እንዲረጋገጥ፣ ለውጥ አደናቃፊዎች በፈጠሯቸው ችግሮች የተጎዱና የተፈናቀሉ የሀገራችን ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥርን በሚያጠናክር መንገድ በዘላቂነት ዳግም የሚቋቋሙበት እና ከችግር ወጥተው ወደቀድሞ ሕይወታቸው የሚመለሱበት መንገድ እንዲዘረጋ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በለውጡ ውስጥ የታዩ ፈተናዎችን በመቋቋም ሕዝባችሁንና ሀገራችሁን በማስቀደም ከፊት ተሰልፋችሁ በመፋለም ላይ ለምትገኙ ብርቅዬ የሀገራችን ልጆች የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያለውን ልዩ አክብሮትና የላቀ ምስጋና ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ኢትዮጵያን ለማበልጸግ የምናደርገው ትግል የማይቀር መሥዋዕትነት እንደሚከፈልበት እናውቃለን፤ በተቻለን ዐቅምም መሥዋዕትነቱን ቀንሰን ወደግባችን ለመጓዝ እንተጋለን፡፡ ምንጊዜም ግን ለተጠቃሚነቱ ሕዝብን ለመሥዋዕትነቱ ራሳችንን እናስቀድማለን፡፡

“ሐሳባችንን ከመድረሻችን፤ እግራችንን ከመንገዳችን ሳንነቅል የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን”!

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ነሃሴ 2012አዲስ አበባ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.