Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በመጭው አርብ የምታመጥቀው ሳተላይት መረጃዎችን በመሰብሰብ ለተቋማት ለማቀበል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በመጭው አርብ የምታመጥቀው ሳተላይት መረጃዎችን በመሰብሰብ ለተቋማት ለማቀበል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ ሳታላይቷን አርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ህዋ ለማምጠቅ ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቃለች።

ስራውን ለመጀመር ከቻይና መንግስት ጋር ስምምነቱ ከተፈረመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሳተላይቷን ለማምጠቅ አራት ዓመታት መውሰዱ ተጠቁሟል።

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፊዚስትና በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተባባሪ ባልደረባ ዶክተር ጌትነት ፈለቀ፥ በታዳጊ ሀገራት ሳተላይት ቴክኖሎጂ ፈጽሞ የማይታሰብ ሆኖ ቢወሰድም፤ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር ግን ወሳኝ በመሆኑ አመለካከቱ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያም ሳተላይትን ማምጠቅ መቻል ትርጉም የሚሰጠው እርምጃ መሆኑንም ነው የሚያብራሩት።

የተለያዩ አይነት ሳተላይቶች እንዳሉ የሚገልጹት ዶክተር ጌትነት፥ ኢትዮጵያ በመጪው አርብ የምታመጥቀው ሳተላይት የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወይንም ሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት እንደሆነ ገልፀዋል።

ሳታላይቷ የምትሰበስበው እና የምታቀበለው መረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታን የሚሰጥ እና ከመረጃ ጥገኝነት የሚያወጣ እንደሆነ ዶክተር ጌትነት አንስተዋል፡፡

በመሬት ምልክታ ሳተላይት ጅማሮውን ያደረገው የሳተላይት ቴክኖሎጂ ዘርፉ ወደ ሌሎች የሳተላይት አይነቶች ማደግ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳተላይት ምርምር ልማትና ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ይልቃል ቻለው፥ ሳተላይቷን ዲዛይን በማድረግ ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ባለሞያዎች መሳተፋቸውን በመግለፅ፤ ይህም ሳተላይቷ ከመጠቀች በኋላ ለሚኖረው ስራ ወሳኝ የሚባል አቅም መፍጠር የተቻለበት ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን 20 ሲሆኑ ÷ ከእነዚህ ውስጥም አምስቱ ሴቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ከቴክኖሎጂ ሽግግር አንፃርም ከፍተኛ አቅም መፍጠር የተቻለበት አጋጣሚ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ሳተላይቷ እንድትመጥቅ ከተደረገች በኋላ የተለያዩ የመሬት መረጃዎችን የምትሰበስብ ሲሆን፥ ሰብስባ የምትልካችውን መረጃዎች ደግሞ ከእንጦጦው የምርመር ማእከል በኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች እየተተነተኑ ለተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚተላለፉ ይሆናል።

በቀጣይ ሶሰት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የመሬት ምልክታ ሳተላይትን የምትልክ ሲሆን፥ ሌሎች የኮሙዩኒኬሽን እና የብሮድካስት ሳተላይቶችን የማምጠቅ እቅድም ተይዟል ብለዋል።

በትእግስት አብረሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.