Fana: At a Speed of Life!

አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ዛሬ ቀጠሮ የያዘ ቢሆንም አቶ ጃዋር መሀመድ አሞኛል ብለው በችሎት በተደጋጋሚ መውጣት እና መግባት የምስክር ሂደቱን ስለሚያስተጓጉል በሚል ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ ጃዋር እንደታመሙ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ንፋስ ለማግኘት ከችሎት ወጥተው የነበረ ሲሆን ዐቃቤ ህግ የምስከሮቹን ጭብጥ እያስመዘገበ ባለበት በድጋሚ ወደ ችሎት ገብተዋል፡፡

ይህ ወጣ ገባ ሁኔታ የዐቃቤ ህግ የምስክር ሂደትን ያስተጓጉለዋል ያለው ፍርድ ቤቱ ለነሃሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌደራል ፖሊስ የማረፊያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር የኔነሽ ገብረእግዚአብሄርም ቀርበው የተጠርጣሪዎችን የአያያዝ ሁኔታ መስተካከሉን እና አምስት ተጠርጣሪዎች ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው የሚገልጽ የህክምና ማስረጃ አቅርበው ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡

አቶ ጃዋር መሃመድ ልጄን እና ባለቤቴን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ላግኛቸው እንዲሁም ከጤናቸው ጋር በተያያዘ የግል ሃኪሜ እንዲያየኝ ይፈቀድልኝ ብለው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የጤናቸው ሁኔታ ባለው የህክምና አሰጣጥ ህክምና እንዲያገኙ እንዲደረግ እና ወጪውን ሸፍነው ከልጃቸው እና ከባለቤታቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲገናኙ እንዲመቻችላቸው እንዲሁም የጤናቸው ሁኔታ ታይቶ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግላቸው አዟል፡፡

ፖሊስም የሁሉንም ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም ተጠርጣሪዎች ከጠበቆች ጋር ለመገናኘት ስንሄድ ድምጽ መቅጃ እና ካሜራ ተተክሏል በሚል ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ ቦታ እንድንገናኝ ይፈቀድልን በሚል አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆች ሚስጢራዊነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲገናኙኝ አዟል፡፡

ዐቃቤ ህግ በሰጠው ምላሽም ሁል ጊዜም በሚስጥራዊ ቦታ ከጠበቆቻቸው ጋር እንደሚገናኙ ጠቅሶ ከካሜራ ጋር ተያይዞ የተነሳውን አቤቱታ እንደማያውቅ እና እንደሚያጣራ አስረድቷል፡፡

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ የቅድመ ምርመራ ምስክር እንደሚሰማ እንደሚያውቁና በቂ መዘጋጃ ጊዜ እንደነበራቸው አስታውሶ ያነሱት ምክንያት የፍትህ ስርአቱን የሚሸረሽር ነው ብሏል።

የተፋጠነ ፍትህ እንዳይሰጥ የተለያዩ እንቅፋቶችን እያነሱ ሂደቱን ወደኋላ ለመመለስ ያለመ ነውም ነው ያለው።

ዐቃቤ ህግ አቶ ጃዋርም ቢሆኑ የህመም ስሜት እንደተሰማቸው መግለጻቸውን ተከትሎ ህክምና እንዲያገኙ ቢጠየቁም አልፈልግም ብለዋል።

እንደማንኛወም ሰው እኩል ህገ መንግስታዊ መብት ነው ያላቸው ይሁንና በግል ሃኪሜ ነው የምታከመው የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ጠቅሷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.