Fana: At a Speed of Life!

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የዓመቱ የአፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ሽልማትን አሸነፉ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የዓመቱ የአፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ሽልማትን አሸነፉ።

ሽልማቱ በአፍሪካ ሊደርሺፕ መጽሄት የሚዘጋጅ ሲሆን፥ በአፍሪካ በ17 የቢዝነስ ዘርፎች ተሸላሚዎችን ይፋ አድርጓል።

ከ220 ሺህ በላይ ሰዎች ለአሸናፊዎቹ በተለያዩ አማራጮች ድምጽ የሰጡ ሲሆን፥ አሸናፊዎቹም በመጪው መስከረም ወር መጨረሻ በሚካሄደው 5ኛው የአሜሪካ-አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ እውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል።

አቶ አህመድ ሺዴም በመጨረሻው ዙር ከቤኒኑ አቻቸው ሮማልድ ዋዳንጊ ጋር የተወዳደሩ ሲሆን በመጽሄቱ ኤዲቶሪያል ቦርድ ምርጫ አቶ አህመድ አሸናፊ ሆነዋል።

አፍሪካ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ስር እንደመሆኗ የቢዝነስ ዘርፍ ሰዎች አህጉሪቱን በመታደግ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

ሁሉም አሸናፊዎች በዓመቱ ለሰሩት ስራና ለአህጉሪቱ ልማት ለሚያበረክቱት አስተዋጽዖ እውቅና ይገባቸዋል፤ ያንንም ሰጥተናል ብሏል መጽሄቱ።

የአፍሪካ ቢዝነስ ሊደርሺፕ ሽልማት በአፍሪካ ቢዝነስ ምህዳር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ኩባንያዎች በየዓመቱ የሚሰጥ ከፍተኛ ሽልማት ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.