Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የቀዳሚ ምርመራ ሂደትን በተመለከተ የሰጠው መግለጫ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው እለት አቶ ጃዋር መሃመድ ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ አቶ ጃዋር መሃመድ አሞኛል በማለታቸው ተሰተጓጉላል።

ከዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን የመስማት ሂደቱን ለማካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዚህ አጋጣሚ ለህዝብ እና ጉዳዩን ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ለማድረግ የምንፈልገው እነ አቶ ጃዋር መሃመድ በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ስር እንደመሆናቸው ጤናቸውን ለመጠበቅ ባለው አሰራር አስፈላጊውን የጤና ክትትል እና አገልግሎት የሚያገኙ እና እያገኙ ያሉ ሲሆን ጤናቸውም በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ለዚህም ማሳያ ከተደረገላቸው ህክምና በተጨማሪ ዛሬ በዋለው ችሎት ምስክር መሰማት እንዳይጀመር የተለያዩ ምክንያቶችን እያነሱ ለረጅም ሰዓት ሲከራከሩ ከቆዩ በኃላ በክርክሩ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ ምስክር መስሚያ ሰዓት ሲደርስ ወጣ ገባ ማለታቸው የሚፈለገው የምስክሮችን የማሰማት ሂደቱን ለማስተጓጎል እና በግብረአበሮቻቸው ሁከት እና አመጽ ለመቀስቀስ ነው።

የተጠርጣሪው ግብረ አበሮች በተለያየ መንገድ ምስክሮችን በማስፈራራት የፍትህ ሂደቱ እንዲስተጓጎል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፍጹም አግባብነት በሌላቸው መነሻዎች እና በተለያዩ ሰበቦች ምስክሮች በቀዳሚ ምርመራ የሚሰሙበት ሂደት እንዲራዘም እና እንዲሰናከል ለማድረግ ጥረት እያደረጉ በመሆኑ እንደ ወትሮው ሁሉ ተቋማችን ለምስክሮች ተገቢውን የህግ ጥበቃና ከለላ የሚያደርግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንፈልጋለን።

ከምንም በላይ በተለያዩ ጥቃቅን ጉዳዮች አላግባብ ከሚቀርቡ አቤቱታ እና ይግባኞች ጀምሮ፣ አልተዘጋጀንም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን፣ ዳኛው ፈገግ ብሏል እና ይቀየርልን በማለት በሰበብ አስባቡ የፍርድ ሂደቱን ለማደናቀፍ በተጠርጣሪዎቹ በኩል የሚደረግ ጥረት እንዳለ ግልጽ ሆኗል።
ይህን እውነታ ህዝቡም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡ እና በአፋጣኝ ፍትህ እንዲረጋገጥ ከምናደርገው ጥረት ጎን እንዲሰለፉ ጥሪያችንን እያቀረብን ማንም ይሁን ማን ከህግ በላይ መሆን የማይቻል መሆኑን በአጽንኦት ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.