Fana: At a Speed of Life!

ብሄራዊ ባንክ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ከባንክ ውጭ በቤትም ሆነ በሌላ ቦታ ማከማቸትን ከለከለ  

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ከባንክ ውጭ በቤትም ሆነ በሌላ ቦታ ማከማቸ ተከለከለ ።

የብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድረስ በቤትም ሆነ በሌላ ቦታ መያዝ እንደሚፈቀድና ከዚህ በላይ ገንዘብ ይዞ መገኘት እንደሚያስቀጣ ይፋ አድርገዋል።

የባንኩ ገዥ ይህን ያሉት ብሄራዊ ባንክ ያወጣቸውን አራት መመሪያዎችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫን በሰጡበት ወቅት ነው።

ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ከባንክ ውጪ ማስቀመጥ መከልከሉም ሀገሪቱ የምታሳትመው የገንዘብ ኖት በተገቢው መልኩ ኢኮኖሚው ውስጥ እንዲዘዋወር ያግዛል ነው ያሉት። በተጨማሪም ህገ ወጥነትን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

የገንዘብ ኖት ባልተገባ ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋሉ ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሬ የምታሳትመው የገንዘብ ኖት እየተበላሸ ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጋትም ዶክተር ይናገር አንስተዋል።

ማንኛውም ሰው ገንዘብ እንዳይጎዳ አድርጎ እንድይዝና የትኛውም አካል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ከባንክ ውጪ እንዳያስቀምጥ፣ ማንኛውም ድርጅት ኤ ቲ ኤም እና መሰል የዲጂታል የግብይት ስርአትን እንዲጠቀም፣

ባንኮች ከውጪ መበደር እንዲችሉ የሚል እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲያድጉ መፈቀዱን የሚገልጹ መመሪያዎችን ነው ብሄራዊ ባንክ ያወጣው።

የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ አበዳሪዎች በውጭ ምንዛሬ እንዲበደሩ ተፈቅዷል ያሉት የባንኩ ገዥ፥ እስካሁን ድረስ ይህ ለኢትዮጵያ ባንኮች የተፈቀደ አልነበረም ብለዋል። መፈቀዱም ለኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገድ ይሆናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሌሎች ኩባንያዎች ከውጭ ለመበደር ሲቸገሩ ይታያል ያሉት ዶክተር ይናገር፥ ይህም የሆነው የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የየወቅቱ አቋም የሚመዘንበት አሰራር ወጥ ስላልሆነ ለውጭ አበዳሪዎች ምቹ ስላልሆነ እንደሆነ አስረድተዋል። ባንኮች ግን ለዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ምቹ ናቸው ብለዋል ዶክተር ይናገር።

የሀገር ውስጥ ባንኮች ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ስርአት ጋር የተሳሰሩም በመሆናቸው በውጭ ምንዛሬ ለመበደር ምቹ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

በዚህም ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ምንዛሬ የሚበደሩት ለሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲያቀርቡ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ማቃለል እንደሚቻል ዶክተር ይናገር ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ግን አላስፈላጊ ስጋቶች እንዳይከሰቱ ብሄራዊ ባንክ ክትትል እንደሚያደርግም አንስተዋል። ይህም ባንኮች ከአቅማቸው በላይ የውጭ ምንዛሬ ተበድረው የሚፈጠር ችግርን ለመከላከል ይረዳል በማለት።

በተጨማሪም በመግለጫው የማይክሮ ኢንሹራንስ ስራን ማንኛውም ሰው እንዲሰራ መፈቀዱ ተገልጿል።

የብሄራዊ ባንክ ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ወደ 13 ሚሊየን ብር ለገበታ ለሀገር መርህ ግብር መለገሳቸውንም ዶክተር ይናገር በመግለጫው ላይ አያይዘው ገልፀዋል።

በካሳዬ ወልዴና ሀይለየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.