Fana: At a Speed of Life!

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚያስገኘውን ሠፊ የልማት ዕድል ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚያስገኘው ዘርፈ-ብዙ የመጠቀም ዕድል የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ፡፡

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ በሚፈጠረው “የሕዳሴ ኃይቅ” ዙሪያ የሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ያካተተ ክልላዊ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ረቂቅ ዕቅድ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት አካሂደዋል፡፡

ስትራቴጂክ ዕቅዱ ግደቡ ሲጠናቀቅ እንደ ሀገር ከሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን ለክልሉ ይዞት የሚመጣውን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚስችል መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ “በለውጡ አመራር በተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ የግድቡ የግንባታ በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑ ሁሉንም አስደስቷል” ብለዋል፡፡

ግድቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኝ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለክልሉ ይዞት የሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የላቀ መሆኑን በመግለፅ በክልሉ ያለውን የመልማት አቅም ከዚህ ዕድል ጋር በማጣጣም ወደ ተጨባጭ ልማት መቀየር የሚያስችል ተገቢ ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ያሉትን ቱባ የባህል እሴቶች፣ የቱሪዝም ሥፍራዎችንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኙ ማድረግ ተገቢ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ ለዚህም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ይዞት የሚመጣው ዕድል ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ዕድል ሳያገኙ የቆዩት የክልሉ ወጣቶች የግድቡ ውኃ በሚተኛበት የደን ምንጣሮ ሥራ መሳተፋቸውን የክልሉ መንግስት አንዱ የሀገራዊ ለውጡ ማሳያ አድርጎ እንደሚያዬውም መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የግድቡ ግንባታ አስኪጠናቀቅ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው አንደሚቀጥሉ ገልጸው ሀገራዊ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ትልቅ የጉብኝት ማዕከል በመሆኑ ክልሉ ከዚህ የሚያገኘውን ጠቀሜታ በአግባቡ ለመጠቀም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ እንደ ሀገር ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር ለክልሉ ልማት ሠፊ ዕድል ያመጣል ያሉ ሲሆን ይህንን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.