Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች በፀረ ሰላም ሀይሎች ተድርጎ የነበረው የአድማ ጥሪ በህዝቡና በፀጥታ አካላት ተሳትፎ መክሸፉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 12 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች በፀረ ሰላም ሀይሎች ተድርጎ የነበረው የአድማ ጥሪ በህዝቡና በፀጥታ አካላት ተሳትፎ መክሸፉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የአሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በውስጥ እና በውጭ ፀረ ሰላም ሀይሎች የሚደረገው የአድማ ጥሪ እና የኦሮሚያ ክልልን የጥፋት ፣ የሁከት እንዲሁም የብጥብጥ ማዕከል የማድረግ ሙከራ የዛሬውን ጨምሮ ለአምስተኛ ጊዜ ጥሪ የተካሄደ መሆኑን በመግለጫው አመልክተዋል።

ሆኖም የጥፋት ሀይሎች ጥሪ ሰላም ወዳድ በሆነው ህዝብ እና በፅጥታ አካላት የጋራ ቅንጅት መክሸፉን ኃላፊው አቶ ጌታቸው ባልቻ ገልፀዋል።

ህዝቡ አሁን ላይ ያለውን የመልማት ፣ የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎችን ሰላማዊ በሆነ መልኩ የሚፈታለትን እንጂ መንገድ የመዝጋት፣ የንግድ እንቅስቃሴን የማቋረጥ እና መሰል ፀረ ሰላም ድርጊቶችን እንደማይቀበል በዛሬው ዕለት በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

ማንኛውንም የአድማ ጥሪ ተከተሎ የኦሮሚያ ክልልን የጥፋት እና የሁከት ማዕከል ለማድረግ ከእንግዲህ በኋላ የሚካሄድ ሰልፍ እንደማይኖርም በመግለጫቸው አንስተዋል።

በክልሉ ማንኛውም ሰው ከህግ በታች መሆኑን እና ላጠፋውም ጥፋት በህጉ መሰረት የሚጠየቅ መሆኑን በመግለፅ ይህንን ለመቀልበስ የሚደረግ ማንኛውም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው መንግስትም የጀመረውን የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ በተጠናከረ መልኩ አንደሚቀጥል እና ህዝቡም እንደወትሮ ሁሉ የአካባቢውን እና የሀገርን ሰላምና ፀጥታ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.