Fana: At a Speed of Life!

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በተጠረጠሩበት ወንጀል ዐቃቤ ህግ በ10 ቀን ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በተጠረጠሩበት ሁከትና አመጽ በማስነሳት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀል አቃቤ ህግ በ10 ቀን ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ብይን ተሰጠ፡፡

መርማሪ ፖሊስ በኢኒጂነር ይልቃል ላይ ሲያከናውን የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን እና መዝገቡንም ለዐቃቤ ህግ መስጠቱን ለችሎቱ ገልጿል፡፡

ዐቃቤ ህግም በስነ ስርዓት ህጉ 109 መሰረት በቂ ማስረጃ ስላለኝ ክስ መመስረቻ 15 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ሲል አመልክቷል፡፡

ኢንጂነር ይልቃል በበኩላቸው እኔ በፖለቲካ ተሳትፎዬ ነው የታሰርኩት ያሉ ሲሆን ÷ የታሰሩበት ቦታ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ መሆኑንም አቤቱታ በማቅረብ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዐቃቤ ህግም የተጠረጠሩበት ወንጀል ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ክስ ቢመሰርት ከ15 አመት በላይ የሚያስቀጣ እና ዋስትና የሚያስከለክል በመሆኑ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

ጉዳዩን የተከታተለው የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎትም የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ዐቃቤ ህግ በ10 ቀን ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ብይን ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኛ፣ የካሜራ ባለሙያ እና ኤዲተር የሆኑ በአጠቃላይ 4 ሁከትና አመጽ ቀስቅሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ዛሬ በድጋሚ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቀዳሚነት ከእስር አያያዝ ጋር በተያያዘ እንዲስተካከል የተሰጠው ትእዛዝ አለመፈጸሙን በመናገር አሁንም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በድጋሚ አመልክተዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በተቻለ መጠን በአያያዝ ላይ ጥንቃቄ እየተደረገ እና ታሳሪዎች እንዲመረመሩ እየተደረገ መሆኑን ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ያከናወነውን ስራንም አብራርቷል፡፡

የምስክር ቃል መቀበሉን፣ ከተለያዩ ተቋማት የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡንና የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን ገልጾ፥ የኋላ ወንጀል ተሳትፏቸውን ለማጣራት ፎቶና አሻራቸውን በማስነሳት ለሚመለከተው አካል ልከናል ብሏል፡፡

ግብረአበሮቻቸውን ለመያዝ የላክነውን የኤሌክትሮኒክስ ምርመራ ውጤት ለማምጣት እና ተጨማሪ የምስክር ቃል ለመቀበል ተጨማሪ 14 ቀን ይፈቀድልኝ ሲል አመልክቷል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ምርመራው ተገቢነት የለውም፣ በአስራት ሚዲያ ከህዳር ወር ጀምሮ በተላለፈ ፖሮግራም እነሱ ሊጠየቁ አይገባም ሲሉ ምርመራውን ተቃውመዋል፡፡

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤት ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ስምንት ቀን ፈቅዷል።

አያያዛቸውን በተመለከተ ለምን ተፈጻሚ እንዳልሆነ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ከእስረኞች አስተዳደር ተወካይ ቀርቦ እንዲያብራራ አዟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.