Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በምስራቅ ሸዋ የሚከናወነውን የመልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 14 ፣ 2012 (ኤፍ. ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ ባለፈው ሰሞን በነበረው ሁከትና ግርገር የተጎዳውን ንብረት መልሶ የማቋቋሙ ስራ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ጎብኝቷል።

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የክልሉን መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ ሲሆን÷ ጉብኝቱ በምስራቅ ሸዋ ባቱ፣ አርሲ ነገሌና ሻሸመኔን ጨምሮ የምዕራብ አርሲ፣ አርሲ እንዲሁም ባሌን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል ።

የልዑካን ቡድኑ ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ባቱ ከተማ በወቅቱ በነበረው ሁከትና ግርገር ውድመት የደረሰባቸውን መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማትና ድርጅቶችን መልሶ የማቋቋሙ ስራ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ በመጎብኘት መጀመሩም ነው የተገለጸው ።

በመቀጠልም ከከተማው ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ህብረተሰብ ክፍሎች የተከሰተውን ድርጊት
ከማውገዛቸውም በላይ እኛን የማይወክል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሁከትና ግርግሩ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችንም መልሶ ለማቋቋም እየሰራን ነውም ብለዋል ።

ከዚያም ባለፈ ህብረተሰቡ የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ያረጋግጥልን ሲሉ የጠየቁ ሲሆን÷በቀጣይም መንግስት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ከጎኑ እንደሚሰለፉ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት ÷የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የተፈናቀሉ ወገኖችና የወደመውን ንብረት ፈጥኖ ወደ ቦታው ለመመለስና ቋሚ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ ብሎም የንግድ ተቋማቱ ጥገና ተደርጎላቸው ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመው ÷ከእንግዲህ ለሚከሰቱ ችግሮች በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተጠያቂ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ጎሳ በበኩላቸው÷ በሁከቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ከክልሉ መንግስትና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በከተማው በመኖሪያ ቤት ደረጃ ጉዳት ከደረሰባቸው 70 ቤቶች ውስጥ 33ቱ በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ መጠገናቸውን አስረድተዋል።

በተመሣሣይ ሁኔታ ጉዳት ከደረሰባቸው 71 የንግድ ተቋማት መካከል 15የሚሆኑት መጠገናቸውን ገልጸው÷በቀጣይም የቀሩትን ለማቋቋም ከክልሉ መንግስትና ህዝብ ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከዚያም ባለፈ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሁከቱና ግርግሩ የተሳተፉ 228 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይም የልኡካን ቡድኑ አባላት በአርሲ ነገሌ እና በሻሸመኔ ከተማ በሁከትና ግርግሩ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ያጽናኑ ሲሆን÷ ጉዳት
የደረሰባቸውን የመኖሪያና የንግድ ተቋማትም ጎብኝተዋል።

በአሁኑ ሰዓትም ከከተማው እና ከአካባቢው ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከከተማው አመራሮች ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ ናቸው።

ህብረተሰቡ በውይይቱ ላይ በተከሰተው ድርጊት ከማዘናቸውም ባለፈ እኛን የማይወክል ነው ሲሉ አውግዘውታል።

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ጉታ ላቾሬ በከተማዋ በተነሳው ሁከት በደረሰው የመኖሪያ ቤትና የንግድ ተቋማት ጥቃት 17 ሙሉ በሙሉ እና 230 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል መውደማቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ውሥጥ 198 የሚሆኑት በህብረተሰቡና በከተማ አስተዳደሩ ጥገና እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

የተቀሩትንም መልሶ ለማቋቋም ከተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ዜጎች ከደመወዝ ማዋጣት ጀምሮ ቆርቆሮ፣ ፍራሽ እና የመሳሰሉትን በማዋጣት ላይ ናቸው ብለዋል።

የህግ የበላይነትን ከማስፈን አንጻርም ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷በዚህም በከተማው በተከሰተው ሁከትም 1250 ተጠርጣሪዎች በያዛቸውን ተናግረዋል ።

ከዚህም ውስጥ 580 የሚሆኑት ላይ ማስረጃ የማጠናቀር ስራ መሰራቱንም ከንቲባው አስረድተዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.