Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አል ሳራጅ መንግስት በሊቢያ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስታቱ ድርጅት እውቅና የተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አል ሳራጅ መንግስት በመላ ሃገሪቱ ከዛሬ ጀምሮ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታወቀ፡፡

መቀመጫውን ሊቢያ ያደረገው የአልሳራጅ አስተዳደር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላትን ሲርጥ ከተማ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንድትሆንም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አልሳራጅም በመላው ሊቢያ የሚገኙ ወታደራዊ ሃይሎችና ታጣቂዎች ከዛሬ ጀምሮ የተኩስ አቁሙን እንዲተገብሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የተኩስ አቁሙ የሊቢያን ሉዓላዊነት ማረጋገጥና በሃገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሃይሎችን የማስወጣት አላማ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጭው መጋቢት ወር በሊቢያ የአካባቢ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድም ጠይቀዋል ነው የተባለው፡፡

እስካሁን በጉዳዩ ላይ መቀመጫውን በምስራቃዊ ሊቢያ ካደረገው የከሊፋ ሃፍጣር ሃይል የተባለ ነገር የለም፡፡

ይሁን እንጅ ሃፍጣር ከዚህ በፊት በተደረጉ የሰላም ድርድሮች በሊቢያ ተኩስ አቁም ቢደረግ እንደሚደግፉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በርካቶችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ ሰላም ለራቃት ሊቢያ ዘላቂ ሰላም ተስፋን የፈነጠቀ ነው ብለውታል፡፡

ምንጭ፣ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.