Fana: At a Speed of Life!

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የትብብር ተምሳሌት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስንተባበር ምን ማሳካት እንደምንችል ያስተማረ ፕሮጀክት ነው” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

አሁን ላይ ግድቡ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ በመሆኑ ዜጎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ቀርቧል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት አባላት የምክር ቤት ፅሕፈት ቤቱን የ2012 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጻምና የ2013 ዕቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።

በዛሬው መድረክ በ2012 በጀት ዓመት በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢ ሥራዎች አማካኝነት ለግድቡ ከ744 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡንና በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል።

የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢኒጂነር ስለሺ በቀለ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ የሲቪል ሥራው 88 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው 46 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የኮርቻ ግድብ ሥራ ደግሞ 99 በመቶ መከናወኑን ጠቁመው በዩኒት ዘጠኝና አሥር የተርባይን ተከላ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የበጋ ወቅት ግድቡን ወደ 595 ሜትር ለማድረስ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በተጠቀሰው ወቅት የ11 ተርባይኖች ገጠማ እንደሚጠናቀቅና በክረምቱ ወቅት ደግሞ ግድቡ 13 ነጥብ 4 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚይዝም አብራርተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ለግድቡ 121 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መውጣቱን ጠቁመው ግድቡን ለማጠናቅቅም የሚፈጀው አጠቃላይ ወጭ 160 ቢሊየን ብር እንደሚሆን ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም በተለይ የሕዝባዊ ተሳትፎ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ግድቡ የአንድ አካል የበላይነትን አስቀርቶ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያሰፈነ በመሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ እየተቸረው መሆኑን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓረቡ ዓለም ጋር የፈጠረችውን ዘመናትን የተሻገረ የንግድ ትሥሥር በመጠቀም ስለግድቡ ያለውን የተዛባ ትርክት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

“ግድቡ ከውኃ ሙሊት ተሻግሮ ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ እየተንደረደረ በመሆኑ የተያዘው በጀት ዓመት ወሳኝ ጊዜ ነው” ያሉት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው።

በየደረጃው ያሉ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅሕፈት ቤቶች የሕዝቡን ፍላጎት የሚመጥን የተሳትፎ ሥልት ሊቀይሱ ይገባልም ነው ያሉት።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የትብብራችን ውጤት ጥሩ መሳያ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግድቡ ፍጻሜ የዜጎች ርብርብ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥልቶች መጀመራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.