Fana: At a Speed of Life!

ህንድ ኢትዮጵያን በጥቃቅን ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 9፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህንድ ኢትዮጵያን በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ልማት ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች።

በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ ከህንድ የመንገድ ትራንስፖርት እና የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሚኒስትር ሽሪ ኒቲን ጋዲካሪ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ትዝታ በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያና ሕንድ መካከል በኢንቨስትመንት፣ በንግድ ፣ በአቅም ግንባታ እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ ለቆየው ግኑኝነታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን ለሚያግዘው የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቁልፍ ነው ብሎ እንደሚያምን በዚሁ ወቅት አንስተዋል።

የህንድ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚቋቋመው ለስራ እድል መፍጠሪያ ማእከል ግንባታ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ይህ ድጋፍ በተለይም ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ልማት ዘርፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካምና የቆየ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

የጥቃቅንና፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ በህንድ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸው፥ የዚህ ክፍል ልማትና እድገት የገንዘብ አቅምን ከማሳደግ ጀምሮ የስራ እድሎችን ለመፍጠር በጣም ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዘርፉ ኢትዮጵያ ለምታከናወነው ስራዎች የህንድን ልምድና ተሞክሮ ለማጋራት ቃል ገብተዋል።

በተጨማሪም ህንድ ለታዳጊ አገራት የሚመች እና አነስተኛ የካፒታል ወጪን በመጠቀም ምቹ የሆነ መንገድ ለመገንባት የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንዳላት ገልጸው፥ በዚህም ዘርፍ በትብብር ለመስራት ሰፊ እድል እንዳለም ጠቁመዋል ።

በመጨረሻም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጎልበት በተጠቀሱት ዘርፎች የሚደረገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ለመቀጠል ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ ደርሰዋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.