Fana: At a Speed of Life!

የአምቦ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ዛሬም አልተጠናቀቀም

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በ532 ሚሊየን ብር ወጪ ከ4 ዓመት በፊት የተጀመረው የአምቦ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ አሁንም አልተጠናቀቀም።

የከተማዋ ነዋሪዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባቀረቡት ቅሬታ፥ ለዓመታት የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት ደረጃ መንገድ እንዲገነባ ሲጠየቅ ቢቆይም ፈጣን ምላሽ አለማግኘቱን አንስተዋል።

በ2008 ዓ.ም የተጀመረው የአምቦ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት ደረጃ መንገድ ግንባታም ከጅምሩ የግንባታው ፍጥነት ዘግይቶ ዛሬም አለመጠናቁን ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት።

መንገዱ ከተማዋን በስድስት ስፍራዎች ውስጥ ለውስጥ በማገናኘት ብቸኛውን የአስፓልት ደረጃ መንገድ አጋዥ ይሆናል ቢባልም፥ በርካታ ምክንያቶች እየተደረደሩ በሚፈለገው ልክ እየተሰራ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።

ግንባታውን የሚያከናውነው የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ኦሊያድ ተፈሪ፥ የውስጥ ለውስጥ መንገዱ መዘግየት ሃላፊነት ሊወስድ የሚገባው አሰሪው አካል መሆኑን ይናገራሉ።

15 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው አጠቃላይ ፕሮጀክት ከስድስቱ ምዕራፎች ሁለቱ ብቻ የወሰን ማስከበር ስራ የተጠናቀቀባቸው መሆኑን ያነሱት ስራ አስኪያጁ፥ ይዞታ የማስከበሩ ስራ ዓመታትን የመውሰዱ ምክንያትም የድርጅታቸው አካባቢው ዝግጁ ሆኖ ባለመረከባቸው የተፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ።

የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ተረፈ በዳዳ በበኩላቸው፥ የከተማ አስተዳደሩ የዲዛይን እና የይዞታ ማስከበር ውስንነቶች እንደነበሩበት ጠቅሰው፥ በችግሩ ዙሪያ በዋነኛነት በወቅቱ የነበረው የከተማ አስተዳደር ተጠያቂ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም 10 ኪሎ ሜትሩን የመንገድ ግንባታ ዝግጁ በማድረግ በ7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩ ላይ ተቋራጩ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል ነው ያሉት።

በቀጣይም ያልተነካውን ቀሪ 5 ኪሎ ሜትር የዲዛይን ችግር በመፍታት መንገዱን ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ደግሞ የከተማዋ ከንቲባ የሚያነሱትን የ5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ዲዛይን ችግር መፍታቱን ይገልፃል።

በኦሮሚያ የመንገዶች ባለስልጣን የኮንትራት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ወንዴ ደሳለኝ፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጅምር ላይ ለሆነው የመንገድ ፕሮጀክቱ የአስተዳደሩ ትኩረት ማጣትን እንደ ችግር አንስተዋል።

ከ22 እስከ 30 ሜትር ስፋት ያለው የአምቦ የውስጥ ለውስጥ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ 532 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦለታል።

በሃይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.