Fana: At a Speed of Life!

አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ ያፀደቀው የገንዘብ ድጋፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛኑን ለማስተካከል ይረዳል- ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ለኢትዮጵያ ያፀደቀው የገንዘብ ድጋፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛኑን ለማስተካከል እንደሚረዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ የ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማጽደቁን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ይህንን ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው “የአይ ኤም ኤፍ ቦርድ የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ የሦስት ዓመት የፋይናንስ ድጋፍ ማሕቀፍን በማጽደቁ በጣም ለማመስገን እወዳለሁ” ብለዋል።

ይህ የገንዘብ ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ኮታ 700 በመቶ የሚበልጥ መሆኑንም ገልፀዋል።
የገንዘብ ድጋፉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛኑን (የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የዋጋ ግሽበት እና የብድር ጫናን) ለማስተካከል የሚረዳ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህ የገንዘብ ድጋፍ ባለ ሀብቶችን እና የሥራ ፈጠራን በማበረታታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በብልጽግና መንገድ ለማስኬድ የሚረዳ እንደሚሆንም ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.