Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በቤተ-እምነቶች ላይ የሚፈጸምን ጥቃት እንደሚያወግዙ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቤተ-እምነቶች ላይ የሚፈጸምን ማንኛውም አይነት ጥቃት እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉትም ሀገር አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን  በዛሬው ዕለት በሰመራ ከተማ በተከበረበት ወቅት ነው።

ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗንና በለውጥ ውስጥ የሚያልፍ ሀገር እንደሚያጋጥመው ሁሉ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከእዚህ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ወደከፍታ ማማ ለማውጣት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።

ለዚህም ሀገራችን ሰሞኑን ወደህዋ ያመጠቀችው የመረጃ መሰብሰቢያ ሳተላይት ከብዙ ተስፋ ሰጪ አመላካች ነገሮች አንዱ ማሳያ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

የምናልማትና የምናስባት የበለጸገች አገር መገንባት የሚቻለው ህዝቦች ተከባብረውና ተፋቅረው በሰላም አብረው መኖር የሚችሉባት አገር  ስንፈጥር ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በማለፍ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ሁሉም የሀገሩን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚገባም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አስገንዝበዋል።

የተለያዩ እምነቶችና ብሔር ብሔረሰቦች ለብዙ መቶ ዓመታት በሰላምና በጋራ አብረው በኖሩባት ኢትዮጵያ በእምነትም ሆነ በብሔር ያለውን ልዩነት መሰረት በማድረግ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“በቤተ-እምነቶች ላይ የሚፈጸም ማናቸውም አይነት ጥቃት ተቀባይነት የለውም፤ የሚወገዝ ተግባርም ነው” ሲሉም ድርጊቱን ኮንነዋል።

አንድ ቡድን የሌላውን አካል መብትና ጥቅም ሲጥስ የራሱን መብትና ጥቅምንም ለመጣስ እድል እየሰጠ መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባም ነው ፕሬዚዳንቷ የገለጹት።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን ላይ ለመሳተፍ በዛሬው ዕለት ሰመራ ከተማ መግባታቸው ይታወቃል።

ፕሬዚዳንቷ በሰመራ ሎጊያ ከተማ ሱልጣን አሊሚራ ሃንፍሬ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባን ጨምሮ የክልሉ ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሰመራ ሎጊያ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በክልሉ ፖሊስ ማርሽ ባንድ የታገዘ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.