Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ በ2012 በጀት ዓመት 122 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2012 በጀት ዓመት 122 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ፡፡
አየር መንገዱ ገቢውን ያገኘው በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ትራንስፖርት መንገደኞችንና ዕቃዎችን በማጓጓዝ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎትና ሆቴል መስተንግዶ በማቅረብ፣ የጥገና አገልግሎትና የአቪየሽን ስልጠና በመስጠት መሆኑ ታውቋል፡፡
በዚህም በ2012 ዓ.ም 149 ነጥብ 72 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 122 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር ወይም የዕቅዱን 82 በመቶ ማሳካት ችሏል ነው የተባለው፡፡
አየር መንገዱ የኮቪድ-19 ተጽዕኖን ተቋቁሞ ይህን ገቢ ሊያገኝ የቻለው በወረርሽኙ የተነሳ የመንገደኞች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሲቀንስ የሕዝብ ማመላለሻ አውሮፕላኖቹን ወደ ጭነት ማጓጓዣ (ካርጎ) በመቀየር በወሰደው እርምጃ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የተለያዩ የወጪ ቅነሳ ስልቶችን በጥናት ላይ ተመርኩዞ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን ሲሆን በዚህም ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማዳን ችሏል ነው የተባለው፡፡
የአየር መንገዱ የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የተገመገመ ሲሆን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረመስቀል አየር መንገዱ የወቅቱ ወረርሽኝ የፈጠረውን የገበያ መቀዛቀዝ የተለያዩ አማራጭ የገቢ ምንጮችንና የወጪ መቀነሻ ስልቶችን አጥንቶ ተግባራዊ ማድረጉ ለጥሩ ውጤት እንዳበቃው ገልጸዋል፡፡
ገቢዎች በተቻለ መጠን በውጭ ምንዛሪ እንዲሆኑና በአንጻሩ የውጭ ምንዛሪ ወጪዎች ደግሞ ሊቀንሱ የሚችሉበት አማራጮች እንዲታዩ፣በጅምር ያሉ ፕሮጀክቶች ሊዘገዩ የሚችሉና ቶሎ መጠናቀቅ ያለባቸው ተለይተው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ያለ ተጨማሪ ወጪ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ጥረት እንዲደረግም አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
እንዲሁም ካለው የገበያ መቀዛቀዝ አንጻር የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ በዓለም ኢኮኖሚ ትስስር ላይ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ሊያስከትል ስለሚችል በጥናት ላይ የተመሠረተ ዕቅድ አስቀምጦ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከኤጀንሲውየህዝብ ግንኙነት ዳይይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.