Fana: At a Speed of Life!

የቴሌኮም ዘርፉን ሪፎርም ለማድረግ ያለመ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቴሌኮም ዘርፉን ሪፎርም ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ውይይት ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በዘርፉ ካሉ ስራ ፈጣሪዎች ጋር እየተካሄደ ነው
ውይይቱ በዋናነት የዘርፉን ሪፎርም አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በየደረጃው ካሉ ባለሙያዎችና ኩባንያዎች ጋር ውይይት እንዲደረግና ዳብሮ ግብዓት እንዲሆን ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ነው፡፡
ዛሬ እየተካሄደ ያለው ውይይት በአዲስ አበባ ብቻ የሚገኙና ከተመረጡ 210 በኢንፎርሜሽን ዘርፍ ከተሰማሩ አካላትና ኩባንያዎች ጋር ነው ተብሏል።
ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ የዘርፉ ተዋንያንም ሃሳባቸውን በአጭር የፅሁፍ መልዕክት የሚሰጡበት እስከ ሰኞ የሚቆይ 6500 አዲስ የሀሳብ መስጫ መስመር ይፋ ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የዘርፉ ተዋንያን በተለይም በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ሪፎርም የሚጠብቋቸውን እና ቢካተትያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ከመሰረተ ልማቶች ጋር ተያይዞ ያሉ ዝግጅቶች፣ ከኢንተርኔት መቆራረጥና የቴክኖሎጂ ስራዎችና ለመተግበር ቀላል ያሏቸውን አሰራሮች ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም ከውጭ የሚመጡ ኩባንያዎችና ድርጅቶች የሚተገብሯቸው ስራዎች በሀገር ውስጥ ያሉ የዘርፉ ተዋንያንና ስራ ፈጣሪዎችን ከገበያው በማያስወጣ መልኩ እንዲሆን ጠይቀዋል።
በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
የቴሎኮም አገልግሎትና ፍላጎት ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ተወዳደሪ ሆኖ ለመቅረብ በሀገር ውስጥ ያሉ የዘርፉ ተዋንያንና ኩባንያዎችን ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንሰራለን ብለዋል።
ይህንንና በቀጣይም ዘርፉን ሪፎርም ለማድረግ የሚደረጉ ውይይቶች፣ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ይሆናልም ነው የተባለው።
በፍሬህይወት ሰፊው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.