Fana: At a Speed of Life!

ፖለቲከኞች እና ህዝቡ ዴሞክራሲን ከመፈለግ ባሻገር ለዴሞክራሲ የሚያስፈልገውን ስነ ምግባር መተግባር ይገባቸዋል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 25 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፖለቲከኞች እና ህዝቡ ዴሞክራሲን ከመፈለግ ባሻገር ለዴሞክራሲ የሚያስፈልገውን ስነ ምግባር መተግባር እንደሚገባቸው ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቷ 5ኛውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት በንግግር ከፍተዋል፡፡

በንግግራቸውም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልተቻለ ዴሞክራሲን ተለማምደን መተግበር አዳጋች መሆኑን ጠቅሰው ዴሞክራሲን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲ የሚጠይቀውን ስራ የሚተግበር ዜጋ እንዲፈጠር ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ ያለፈው ዓመት ስኬቶች የተመዘገቡበት ዓመት መሆኑን ጠቅሰው በአንጻሩ በህዝብ ጽናት የተደቀኑ ችግሮች የታለፈባቸው እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡

ከስኬቶቹም መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምስራቅ አፍሪካ ላደረጉት ጥረት እንዲሁም ለ20 ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ወደ ሰላም እንዲመለስ ማድረጋቸው አንስተዋል፡፡

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት ዳግም በማደስ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በህዳሴ ግድብ ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቁንም አንስተዋል፡፡

እንዲሁም በቴክኖሎጂው ዘርፍ የመጀመሪያውን ሳተላይት ማምጠቅ መቻሉ ከስኬቶቹ መካከል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከምርጫ አንጻርም አዲስ የምርጫ አዋጅ በማጽደቅ እንዲሁም የሲዳማ ክልል ሂደትን በስኬት በማጠናቀቅ ለመጭው ምርጫ ዝግጁነቱን ያሳየበት ነበር ብለዋል፡፡

ከኢኮኖሚ አንጻርም ባለፈው ዓመት ሦስት ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ማግኘታቸውን አንስተው ኮሮናን በመከላከል ረገድ ስኬታማ ስራ መሰራቱንም አውስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ማህበራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ህዝቡን ያሳተፈ ስራ የተሰራበት እንዲሁም ለተለያዩ ሃገራት የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ የተደረገበት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ከፕሮጀክት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለዓመታት ሲጓተቱ ለነበሩ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በስኬት የተጠናቀቁበት ዓመት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ያለፈው ዓመት ህገ መንግስቱን ከማጠናከር አንጻር ሃገሪቱ አይታ የማታውቀው የህገ መንግስት ትርጉም ልምምድ ውስጥ እንደገባችም ነው ያነሱት፡፡

በአንጻሩ የፖለቲካ ምህዳሩ በስሜትና በጉልበት ውስጥ ወድቆ እንደነበር ያነሱት ፕሬዚዳንቷ በዚህም በተፈጠሩ ግጭቶች የዜጎች ህይዎት የጠፋበትና ብሎም የተፈናቀሉበት፣ ያልተገቡ የህግ ጥሰቶች የተፈጸሙበት ዓመት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በኢኮኖሚው መስክም ካለፉት አመታት በተሻለ የወጪ ንግድ ገቢ የተገኘበት ስኬታማ አመት እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ ባለፈም 5 ቢሊየን ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እቅድን ማሳካት ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ኮሮናን በመከላከል ረገድ አፋጣኝ የመከላከል አቅም የተገነባበት መሆኑ፣ በኮሮና ምክንያት የሚፈጠረውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም ምንም መሬት ጦሙን እንዳያድር ማድረግ የተቻለበት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በአንጻሩ በኮቪድ19 ምክንያት የሃገራዊ ምርጫ መራዘም፣ የበረሃ አንበጣ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያደረሰው ጉዳትን ጨምሮ ሌሎች አጋጣሚዎች ከስኬት ባሻገር የታዩ ችግሮች ነበሩ ብለዋል፡፡

በ2013 ኮሮና የሚፈጥረውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም እንደሚሰራ አውስተው ወረርሽኙ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ እንዲሁም ወረርሽኑ ሲያልፍ ኢኮኖሚው በተገቢው ፍጥነት እንዲያገገም ይሰራልም ነው ያሉት በንግግራቸው፡፡

በመረጋጋት ላይ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲቀጥል እንዲሁም የዋጋ ግሽበቱ ላይ በተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ጥብቅ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ ለማስፈጸም መታቀዱንም አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ የግብርና ሜካናይዜሽን የገጠር ፋይናንስ ማሻሻል እና የግብርናውን ዘርፍ በደንብ ማሻሻል በዚህ ዓመት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ለዓመታት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ የአረንጓዴ አሻራን በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል፣ የቱሪዝም ሴክተሩን ለማነቃቃት በቅርቡ የተሰሩ ፓርኮችን መነሻ በማድረግ የተለያዩ የቱሪዝም ፓርኮችን መገንባት የበጀት አመቱ እቅድ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.