Fana: At a Speed of Life!

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የቀብር ስነ ስርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈፀመ።

የቀብር ስነ ስርዓታቸው ከመፈፀሙ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሚገኘው ልደት አዳራሽ የአስክሬን ሽኝት ተካሂዷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ሽመልስ አብዲሳ፣  ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሚኒስትሮች ፣ ቤተሰቦቻቸው ፣የቀድሞ የስራ ባልደረቦቻቸው ፣ ታዋቂ ሰዎች እና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት  የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈፅሟል።

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የህይወት ታሪክ ተነቧል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የኢትዮጵያዊነትን ሀሳብ የሚያቀነቅኑ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ሠብዓዊ መብቶች መከበር ባደረጉት ትግልም አሻራቸውን ያሳረፉ እንደሆነም ይነገርላቸዋል።

በረጅም ጊዜ የአካዳሚክ ሕይወታቸውም በድርቅና ረሃብ፣ በማህበራዊና ሌሎች መስኮች ጥናትና ምርምሮችን አካሂደዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ደራሲ፣ ፖለቲከኛ፣ የጂኦግራፊ መምህሩ ፕሮፌሰር በህይወት ዘመናቸው የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና መፃኢ ተስፋን በተመለከተ ሃሳባቸውን ለትውልድ ሲያጋሩ ቆይተዋል።

ከዚህ ባላፈ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ( ኢሰመጉ) መስራች ናቸው።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ባደረባቸው ሕመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.