Fana: At a Speed of Life!

የመረጠን ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ ሃላፊነታችንን መወጣታችንን እንቀጥላለን- የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ ፣መስከረም 26 ፣2013 ( ኤፍ.ቢ.ሲ) የመረጣቸው ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ የተቀበሉትን ህዝባዊ ሃላፊነት መወጣታቸውን እንደሚቀጥሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የኮሮናወረርሽኝ የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር ምርጫ እስከሚካሄድና የመረጣቸው ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ የተቀበሉትን አደራ መወጣታቸውን እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

ከመስከረም 25 በኋላ የምክር ቤቱ ህጋዊነት ላይ በአንዳንድ አካላት የሚነሱ ሃሳቦች የሕገ መንግስት መሰረት የሌላቸው መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላትን ሕዝብ አምኖ የመረጣቸውና የበርካቶችን ውክልና የያዙ በመሆናቸው ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ ማገልገላችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

በመሆኑም መንግሥት ያወጣቸውን አሰራሮች ተግባራዊነት በመከታተል አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠርና የመከታተል ሥራችንን እንቀጥላለንም ነው ያሉት።

በምክር ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ÷ 6ኛው ብሄራዊ ምርጫ ቀደም ሲል ሊካሄድ ወጥቶ የነበረው መርሃ ገብር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን አስታውሰዋል።

ምክር ቤቱ የሕዝብን ደህንነት በማስቀደም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ደረጃ በደረጃ ተከትሎ ምርጫውን ማራዘሙንም አብራርተዋል።

የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያሳለፉትን ውሳኔ መተግር የአስፈጻሚ አካልና የሁሉም ክልሎች ግዴታ መሆን እንዳለበትም በግልጽ ይታወቃልም ነው ያሉት።

በመሆኑም የአገሪቱን ህገ-መንግስት በመጻረር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተወከሉበትን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በመጣስ የተካሄደ ምርጫ ህገ ወጥ መሆኑን ገለጸዋል።

ምክር ቤቱ የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሰረት በ2013 ዓ.ም ምርጫው እንዲካሄድ ሲወስንም የህዝብን ጤና አደጋ ላይ ሊጥሉ የማይችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን ከመረመረ በኋላ መሆኑን አስንተዋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ÷ መንግስት እያከናወነ ያለውን የምጣኔ ሃብት፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ የለውጥ ተግባር በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በህገ መንግስቱ መሰረት መንግስት የሚያወጣቸውን እቅዶች ተፈጻሚነት ክትትልና ድጋፍ ይቀጥላሉም ሲሉ ተናግረዋል።

ከመስከረም 25 በኋላ ህጋዊ መንግስት የለም በሚል አንዳንዶች ለሚያናፍሱት ወሬ ህዝቡ ሊደናገር እንደማይገባው ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.