Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ሽብር ሲፈጥሩ በነበሩ የጥፋት ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሰሞኑ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ጉብላክ ቀበሌ በንጹሃን ዜጎች ላይ ሽብር ሲፈጥሩ በነበሩ 14 የጥፋት ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ጋሹ ዱጋዝ በተጨማሪም ሁለት ግለሰቦች ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው መያዛቸውን ተናግረዋል።

በተወሰደው እርምጃም 5 የክላሽ የጦር መሳሪያዎች እና 10 ኋላ ቀር መሳሪያዎች መያዛቸውን ነው የገለጹት።

ከሁለት ቀናት በፊት በዳንጉር ወረዳ ጉብላክ ቀበሌ 14 ንጹሃን ዜጎች በአጥፊዎች የተገደሉ ሲሆን 8ቱ ደግሞ ቆስለው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል ኃለፊው።

የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ንጹሃን ሰዎች መካከል አንደኛው የውጭ ሀገር ዜጋ መሆኑን አቶ ጋሹ ዱጋዝ ገልጸዋል።

በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ በመንቀሳቀስ ቀጠናውን ለማዋከ በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ በጋራ በመስራት የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቀጠናውን ከጠላት ነጻ ለማድረግ በዞኑ ውስጥ ተደጋጋሚ ግጭት በሚስተዋልባቸው ዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች ውስጥ በተለይ ገጠር አካባቢ የሚኖረው አርሶ አደር ለግብርናም ሆነ በማናቸውም ጉዳዮች እንዳይንቀሳቀስና ላልተወሰነ ጊዜ ባለበት ማዕከል ተረጋግቶ እንዲቆይ አቅጣጫ ተቀምጧልም ነው የተባለው።

የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ዳንጉርና ጉባ ወረዳዎች የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እንዳይደረስ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በሁሉም የጸጥታ አካላት አማካኝነት በማጀብ ጥቃት እንዳይደርስ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።

የዞኑን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በመደምሰስም ሆነ ወደ ህግ ለማቅረብ በኩል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው የገለጹት።

በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች በተለያየ ጊዜ ተፈናቅለው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ወደ ነበሩበት ቀዬ የማስመለስ ስራዎችም እየተሰሩ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የክልሉ መንግስት በዞኑ ውስጥ በተደጋጋሚ በሚስተዋለው ግጭት ላይ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ እና በቸልተኝነት በተመለከተ በ45 አመራሮች ከኃላፊነት እንደተነሱና 15ቱም ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ ይታወሳል።

በመጨረሻም የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው የቅድመ ወንጀል መከላከል ስራ ህብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲወጣ ሃላፊው ጥሪ ማቅረባቸውን ከመተከል ዞን ኮሚኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ወረዳ አንድ 45 ሺህ ሀሰተኛ የኢትዮጵያ የብር ኖት መያዙን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈትቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር በላቸው ፈረደ እንደገለፁት÷ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቱ በቁጥጥር ስር የዋለው በአሶሳ ከተማ ወረዳ አንድ ቀጠና 3 መነሃሪያ አካባቢ በአንድ መኝታ ክፍል ውስጥ ነው።

ግለሰቡ አልጋ ይዞ ካደረበት ክፍል አስቀምጦ እንደጠፋ የመኝታ ክፍሉ ባለቤት ለፖሊስ በሰጠው መረጃ መሰረት 45 ሺህ ሀሰተኛ የብር ኖት በቁጥጥር ስር ውሏል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.