Fana: At a Speed of Life!

ለጎሃፅዮን(ቀሬጎአ) ደጀን መንገድ ከባድ ጥገና ሊደረግለት ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለጎሃፅዮን(ቀሬጎአ) ደጀን መንገድ ከባድ ጥገና ሊደረግለት መሆኑን አስታወቀ፡፡
40 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የጎሃፅዮን(ቀሬጎአ) ደጀን አስፋልት ኮንክሪት መንገድ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች አማካኝነት አደጋ እየደረሰበት መሆኑን ባለስልጣኑ በስፍራው ባደረገው ቅኝት መመልከት ችሏል፡፡
በተለይም ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጡ አስቸጋሪነት ጋር ተዳምሮ በክረምቱ የጣለው ከባድ ዝናብ የመንገዱ አካል በሆነው አባይ በረሃ ላይ የመሬት መንሸራተት እና ናዳ ማስከተሉንም ገልጿል፡፡
ከባድ ተሽከርካሪዎችም ለመንገዱ መበላሸት አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ኤልያስ ተክለወልድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል።
ይህን ተከትሎም ባለስልጣኑ የትራንስፖርት ፍሰቱ እንዳይስተጓጎል አሁን ላይ አፋጣኝ የጥገና ስራ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመንገዱ ላይ እያጋጠመ ያለው ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲኖረው ለማድረግም በፕሮጀክት ታቅፎ በከባድ ጥገና ደረጃ እንዲገነባ ተወስኗልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከመንገዱ አጠቃላይ ክፍል በእጅጉ የተጎዳውን 10 ኪሎ ሜትር በቅድሚያ በአስፓልት ደረጃ ከባድ ጥገና በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት 60 ሚሊየን ብር የጥገና ወጪም ተመድቧል።
ስራውን ለመጀመርም የግንባታ ግብዓቶችን የማሟላት ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ስራውን በተያዘው በጀት አመት ለማጠናቀቅም ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
መንገዱ ባህርዳርና ጎንደርን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን ከአዲስ አበባ ጋር ከማገናኘቱም በላይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ከሚያገናኙ የወጪ ገቢ መዳረሻ መንገዶች መካከል አንደኛው ነው፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.