Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት የልህቀት ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጋዜጠኞችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግ የልህቀት ማዕከል እንደሚገነባ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።
የማዕከሉን ግንባታ ከሶስት ዓመት እስከ ሶስት ዓመት ከግማሽ ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ መታቀዱም ነው የተገለጸው።
በኢትዮጵያ በ13 ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነት ትምህርት እንደሚሰጥ መረጃዎችያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም÷ የዩኒቨርሲቲዎቹ የጋዜጠኝነት ስርዓተ ትምህርት ተመሳሳይነት ያለውና አንዱ ከአንዱ እየገለበጠ እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሰጡ የተግባር ትምህርት ደካማ መሆን፣ ለሥራው የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማት አለመሟላትና ትምህርቱ በብቁ ባለሙያዎች ባለመሰጠቱ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች የሙያ ክህሎት ችግር ያጋጥማቸዋልም ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ የጋዜጠኝነት የልህቀት ማዕከል እንደሚገነባም አመላክተዋል።
ማዕከሉ ምሩቃን በሥራ ላይ ሆነው ሙያዊ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ድጋፍ እንደሚያገኙበትም አስረድተዋል።
ባለስልጣኑ ማዕከሉ የሚቋቋምበት ትልመ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) ከኳታር መንግሥትና ከአልጄዚራ ብሮድካስት ማሰራጫ ጋር ባለፈው ዓመት ማዘጋጀቱንም ነው የ ገለጹት።
በትልመ ሀሳቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ተካተውና ዳግም ተዘጋጅቶ መላኩንም አስታውቀዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱንና ሥራዎች በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄዱ ተጽዕኖ ማድረሱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰው÷ ለማዕከሉ የሚያስፈልግ ቦታ በመለየት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው በጀት በኢትዮጵያና በኳታር መንግሥታት እንደሚሸፈን አመላክተዋል።
አቶ ወንድወሰን አያይዘውም ማዕከሉ የብሮድካስትና የሕትመት መገናኛ ብዙኃን የሚያስፈልጉት መሰረተ ልማት እንደሚኖሩትና የሃገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና ይሰጥበታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.