Fana: At a Speed of Life!

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ገለጹ ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ÷ የፍትህ ተቋማትን ለማሻሻል እና ህግን ለማስከበር የተጀመሩ ስራዎች በቀጣይም ትኩረት የሚሰጣቸው ሃገራዊ ጉዳይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጉዳዮ ዙሪያ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸዉ የህግ ምሁራን በበኩላቸው፥ ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ማረቅ እና የፍትህ አካላትን ገለልተኛ እና አቅም ያላቸው ለማድረግ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍ ህግ መምህር አቶ ደጀኔ የማነ፥ በህግ ማስከበር ሂደት ከፊት የሚቀድመዉ ወንጀልን ቀደሞ የመከላከል ስራ ክፍተቶች ያሉበት እንደሆነ አንስተዋል።
አቶ ደጀኔ በቅርብ ጊዜያት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የታዩ የህግ ጥሰቶችን ለአብነት ያነሱ ሲሆን÷ የህግ ጥሰቶች ከተፈጸሙ በኋላ ጥፋተኞችን በአግባቡ ተጠያቂ የማድረግ እርምጃዎችም ቢሆኑ ክፍተት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።
የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ውብሽት ግርማም፥ ወንጀልን በመከላከል ደረጃ የሚነሱ ክፍተቶች ስለመኖራቸው ይስማማሉ፡፡
ይሁን እንጂ ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት መሻሻል የታየባቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
መንግስት ካለፉ ጥፋቶች የሚማርበት እና የሚያስተካክላቸዉ በርከት ያሉ የቤት ስራዎች እንዳሉም የህግ ባለሙያ እና ጠበቃው ያምናሉ።
የህግ ባለሙያዎቹ የፍትህ አካላት እናገለግለዋለን ለሚሉት ህዝብ ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጡ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዜጎች በፍትህ ተቋማት ላይ አመኔታ ይኖራቸዉ ዘንድ ተቋማቱን ገለልተኛ እንዲሁም አቅም ያላቸው ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ፥ የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር በተያያዘ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በመልካም ጎናቸዉ ሊነሱ እንደሚገባ ያስረዳል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፥ በባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ የህግ ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማስፈን በበርካታ መዝገቦች ላይ ክስ ስለመመስረቱ ነው ያነሱት።
ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት የፍትህ አካላት አሁን ላይ እያሳዩት በሚገኘው መሻሻል ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ስለመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገልጿል።
ይህም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያለው ቁርጠኛ አቋምን ያሳየ ነው የሚሉት ዶክተር ጌዲዮን፥ በቀጣይም ቢሆን ህግ የማስከበሩ ጉዳይ ለነገ የሚተው የቤት ስራ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
በአወል አበራ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.