Fana: At a Speed of Life!

የጥምቀትን በዓል ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በዓሉ ሀይማኖታዊና ትውፊታዊ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር ከማድረግ ጎን ለጎን ለከተማዋ ዘላቂ እድገት አስተዋጽኦ የሚኖራቸው የውይይት ፕሮግራሞች እንደሚኖሩ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም ተናግረዋል፡፡

ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉባቸው በቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና በሰላም ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱም ነው የተገለፀው፡፡

በሀገራዊ ሰላምና አብሮነት የማይተካ ሚና የሚጫወቱት የሀገር ሽማግሌዎች ያለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ለማመቻቸት የሀገር ሽማግሌዎች ህብረት ምስረታም እንደሚከናወን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም ከመላ ሀገሪቱ የሀገር ሽማግሌዎች ጎንደር እንደሚገቡ ነው የተነገረው፡፡

በጎንደር የሚከበረውን ጥምቀት በሚያደምቀው የባህል ሳምንት የአካባቢውን ባህልና ገጽታ የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ትዕይንቶችና የመዝናኛ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

በሃይማታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች በድምቀት በሚከበረው በዓል ከ100 ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችና እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡

አምባሳደሮችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በበዓሉ ላይ እደሚታደሙ የገለጹት ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም፥ ለኢትጵያዊያን፣ ለትውልድ ኢትጵያዊያን፣ ለኤርትራዊያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ በበዓሉ እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የጎንደር ከተማና አካባቢው ሰላም ወደ ቀደመ ሁኔታው በመመለሱ የጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡

የመምሪያው የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አስቻለው አዲሱ እንደገለጹት ፥ጎንደር ከተማና አካባቢው ወደ ቀደመ ሰላምና መረጋጋት በመመለሱ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

በህዳር ወር ብቻ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቁጥር በ68 በመቶ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር ደግሞ በ60 በመቶ ማደጉን አቶ አስቻለው ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት ጎንደር ከተማና አካባቢውን ከጎበኙ 13 ሺህ 359 የውጭ ሀገር ጎብኝዎች 2 ሚሊየን 624 ሺህ ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን፥ በተመሳሳይ ወቅት ከ52 ሺህ 189 የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 419 ሺህ 356 ብር ገቢ መገኘቱን ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጎንደርን እየጎበኙ መሆኑን ያነሱት አቶ አስቻለው ያለስጋት በራሳቸው ተሸከርካሪ ከጎንደር ባህርዳር በመጓዝ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው የአካባቢው ሰላም አስተማማኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በነብዩ ዮሐንስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.