Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ ከዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ ነፃ በሆነችበት የድል አመት የፖሊዮ በሽታ ቀንን በማክበራችን የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የፖሊዮ ቀን ለየት ያደርገዋል- ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አህጉራችን አፍሪካ ከዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ ነፃ በሆነችበት የድል አመት የፖሊዮ በሽታ ቀንን በማክበራችን የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የፖሊዮ ቀን ለየት ያደርገዋል ሲሉ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ይህንን የተናገሩት የዓለም የፖሊዮ ቀን ”ስኬቶቻችንን በማስቀጠል ፖሊዮን ጨርሶ ለማጥፋት እርምጃ እንውሰድ ” በሚል መሪ ቃል በተከበረበት ወቅት ነው።

በኢትዮጵያ እና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ ጊዜ ተከስቶ የነበረውን የፖሊዮ በሽታ ስርጭት ለመግታት በጤና ሚኒስቴር እና በአጋር ድርጅቶች ትብብር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ዶክተር ሊያ ገልፀዋል።

ለአጭር ግዜ ቢሆንም የኮቪድ 19 አለም አቀፍ ወረርሸኝ የፓሊዮ ክትባት ዘመቻ ለማካሄድ ተግዳሮት ሆኖብን ቢቆይም በኩፍኝ ክትባት ዘመቻ የተገኘውን ልምድ በመጠቀም የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ዘመቻው እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭነት ባለባቸው ክልሎች በኦሮሚያ፣በደቡብ፣ በሶማሌ ፣ አዲስ አበባ እና በሀረሪ ክልሎች በመካሄድ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሁለተኛው ዙርም በእነዚሁ ቦታዎች በቅርቡ እንደሚጀመር የገለፁት ዶክተር ሊያ ÷ ይህንን በመረዳት ወላጆች የመደበኛ መርሃ ግብር ክትባቶችን እና በዘመቻ የሚሰጡ ክትባቶችን ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስትሯ አያይዘውም የጤና ሚኒስቴር የፖሊዮ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው ÷በቀጣይ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ማኅበረሰቡ፣ ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በፖሊዮ ማጥፋት ስራዎች ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ እና ድጋፍ እንዲያደርጉ የአደራ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.