Fana: At a Speed of Life!

ትውልድ ላይ ያጠላው የስፖርት ዉርርድ ጨዋታ ‘ቁማር’ ሱስ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ እሁድ ቀን ነው፤ ምሽት አንድ ሰኣት አካበቢ ወደየቤቱ ሊገባ የጓጓን ተሳፈሪ የጫነዉ ታክሲ ትርፍ በተጫኑ ሰዎች ሞልቷል ።

ከአጠገቡ ያለን  ክፍት ቦታ የጠቆመኝ ልጅ ጎን ሄጄ ተቀምጫለሁ፤ በግምት 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለ ወጣት ነዉ።  

የስማርት  ስልኩን እየነካካ በቁጭት ሲወራጭ ተመለከትኩት።

አዎን፤ በሳምንቱ መጨረሻ የነበረ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ውጤት፣ በመደበው 50 ብር 3 ጨዋታዎችን ገምቷል።

ለመቆጨቱ ምክንያት ከሶስቱ በአንዱ መሸነፉ እና ሊያገኝ የጓጓለትን በሺዎች ብር ማጣቱ ስለመሆኑም አጫውቶኛል ።

ለሱ ይህ ተግባር፤ ከቀን ገቢው ዘግኖ የሚያስቀርለት ልማዱ ሆኗል።

 “ቢያንስ የቀን ገቢ ይሆናል፣ ምን ሳታገኝና የሆነ ነገር የምታገኝበት ነገር ይኖራል እንጂ ኪሴ ባዶ አይሆንም፣ የምፈልገዉን ነገር አደርጋለሁ፣ ብር ሳገኝ ብቻ ነዉ     የምቆርጠዉ፣ አሁን ለምሳሌ 100 ብር ከቆረጥኩኝ ኪሴ ላይ ሌላ መቶብር ከሌለ በ30 ብር እንኳን ልቁረጥ ብዬ አልሄድም፤ ሁለት መቶ ብር ኖሮኝ መቶ ብር  ብቆርጥ ግን ችግር የለዉም፤ ለምን መሰለህ መቶ ብሩ ጠፊ እንደሆነ ስለማዉቀዉ ብቆርጥበትም ችግር የለዉም”

በዚሁ ውርርድ እንደሚሳተፍ የነገረኝ ሌላዉ ስሜ ይቆይ ያለኝ ወጣትም፣ ገንዘብ በያዘበት አጋጣሚ ሁሉ በውርርዱ እንደሚሳተፍ ይናገራል።

እርሱ በሚወራረድበት አካበቢ የሚያሸንፉ ወጣቶች ጥቂት መሆናቸዉን ያነሳል።

በዚህ ተግባር ውስጥ ግን፤ ሀሳብና ጭንቀት፣ ደግሞም ሲሸነፍ ሌላ ቀን አሸንፋለሁ የሚል እልክ ውስጥ መግባት፣ ሱስ ዉስጥ እንድንገባ ያደርገናል ብሎ ያምናል፤ ይህንን እያወቀም ግን መወራረዱን ቀጥሏል ።

“ብር ባገኘሁ ቁጥር እጫወታለሁ፣ ይገርምሀል ከሀያ ብር ጀምሮ ነው የምትቆርጠው፣ ከ20 ብር ጀምሬ እስከ 500 ብር ድረስ ቆርጬ አዉቃለሁ ስንት ለስንት አለቀ እያልክ ለሊት ላይ ብንን የምትለዉ ነገር፤ ከዛ ነገ ስትመጣ ደግሞ የሆነ ብር ሳታገኝ ዛሬ ባላገኛቸዉ ነገ አገኛቸዋለሁ ብለህ ታስባለህ፣  በዚህ ተነሳስተህ ስትቆርጥ ሱስ እየሆነብህ ይመጣል ማለት ነው፤ ገንዘብ ባገኘህ ቁጥር ዛሬ ኳስ አለ እቆርጣለሁ ካልክ ይሄዉ ነገር ሱስ እየሆነብህ ነዉ፣ ኳሱ ቢቆም፣ ኳሱ ይቆማል ሱስ አይሆንም ትላለህ፣ ኳስ ግን ቀጣይነት ያለዉ ነገር ነዉ ስለዚህ ባየህ ቁጥር ደግሞ መቁረጥ አለብህ ማለት ነው፤ ገንዘብ ኪስህ ዉስጥ ካለ በተለይ አያስችልህም”

በዚሁ የውርርድ ጨዋታ ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችም ሆነ የታዳጊዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ያነጋገርኳቸዉ ሰዎች ነግረውኛል ።

የዉርርድ ተቋማት ተብለዉ ህጋዊ ፈቃድና እዉቅና የተሰጣቸዉ ድርጅቶች፣ የዳበሩ ድረገፆች ያሏቸዉ፣ አማራጭ የአንድሮይድ መተግበሪያን መጠቀማቸዉ እና አለፍ ሲልም ይህ ላልገባቸዉ  በአዲስ አበባ እና በክልሎች የተለያዩ ቦታዎች የመወራረጃ ትኬትን መሸጣቸው ወጣቶች እና ታዳጊዎችን በቀላሉ እንዲይዙ አድርጓቸዋል።

የመወራረጃ አማራጮቹም አነስተኛ ከተባለው 10 ብር እስከ ተወራራጁ አቅም ድረስ የሚፈቅደዉ መሆኑ ፣ በሱስ ለሚያዘዉ ሰው የፈለገዉን ያደርግ ዘንድ በር ይከፍታል።

የሶሻል ሳይኮሎጂ ባለሙያ እና በሲቪልሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ቁምነገር ፍቅሬ እንደሚሉት ግን፥ ነገሮች ወደሱስ መቀየራቸውን የምንለካዉ በገንዝቡ ከፍታ አልያም ዝቅ ማለት አይደለም።።

“የመጠጥ ሱሰኛ የሆነ ሰው የመጀመሪያ ቀን ስለጠጣ አይድለም ሱሰኛ የሆነው፤ እየደገመዉ ሲሄድ ነው አይደል፤ ልክ ሌላም ሲጋራም ጫትም ብትወስድ እና ልክ እንደዚህ ሁሉ ሱስ ላይ ደረሰ የምንለዉ የቁማር ጨዋታም፤ እየተደጋገመ እየተደጋገመ ይሄድና የሆነ ሰኣት ላይ ሱስ ይሆናል፤ ለምሳሌ አሁን ወጣቱን ብታየዉ እንደአንደኛዉ ስጋት ብታየዉ ስጋት አደርገህ ልታየዉ ትችላለህ፤ አሁን ላይ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞም ነው ማለት ኢንተርኔት ተደራሽነት በሰፋ ቁጥር የኤሌክትሮኒክ ባንኮች እየሰፉ በመጡ ቁጥር ከማያውቋቸዉ አካላት ጋር ሁሉ ውርርድ እየተካሄደ ነዉ” ይላሉ ወይዘሮ ቁምነገር።

በርግጥም በሀገራችን ፈቃድ ተሰጥቷቸዉ ከሚንቀሳቀሱት ከሚያወራርዱ ድርጅቶች በሶስቱ ያደረጉት ቅኝት  ለውርርድ የሚቀርቡት አማራጮች ተዋቂዎቹ ሊጎች ብቻ አይደሉም፤ እንዲያዉም በሀገራችን እምብዛም ታዋቂነትና አድናቂ የሌላቸዉ የጨዋታ አይነቶችም ጭምር እንጂ።

የስፖርት ክፍል ባልደረባችን ጋዜጠኛ አላዛር አስገዶም እንደሚለው፥ በሀገራችን ብዙ ተመልካች ያላቸዉ 5ቱ የአዉሮፓ ትልልቅ ሊጎች፣ በእንግሊዝ፣ ስፔን፣ የጣሊያን፣ ጀርመንና ፈረንሳይ የሚከወኑት ነዉ ሲል ይሄዉ የውርርድ እንቅስቃሴ ከዚሁ የወጣ መሆኑን እንኳን ብናይ ግን ከእግርኳስ ጨዋታ ፍቅርና አድናቂነት ያፈነገጠ ለመሆኑ ማሳያ ሊሆነን ይችላል ይላል ።

አላዛር አስገዶም፥ የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ለምሳሌ በሳምንት ነዉ ጨዋታዎች የሚደረጉት፤ የአዉሮፓ ጨዋታዎችን የምታካትት ከሆነ ምንአልባት አንድ ክለብ (ቡድን) በሳምንት ሁለት ጨዋታ ሊያደርግ ይችላል እንጂ በየእለቱ ጨዋታ የለም ግን ዝም ብለህ የአለም ሊጎችን ብታይ በየቀኑ የተለያዩ ሊጎች ላይ ጨዋታ ሊኖር ይችላል እና በየእለቱ የሚወራረዱ ሰዎች አሉ የእስራኤል ክለቦችን ማካቢቴልአቪቭ የሚባል ክለብ ብዙ ሰዉ አያውቅም ወይም ቤርሺባህ የሚባል ክለብን ብዙ ሰዉ አያዉቅም ወይ ቱርክ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ዉስጥ ያሉ ክለቦችን ብዙ ሰዉ አያዉቅም ግን እነዚህ ክለቦች ጭምር ለውርርድ ሰዎች ይሄኛዉ ክለብ ያሸንፋል ብለዉ ሲወራረዱ እናያለንና በእግር ኳስ ካርታ ውስጥ የሌሉ በቴሌቪዝን ስርጭት የማናያቸዉ በእኛ ሀገር ተወዳጅ ከሆኑ ሊጎች ውጭያሉ ሀገራት የሚገኙ ሊጎች ውስጥ ጭምር ዉርርዱ ይደረጋል፤ አፍጋኒስታን ውስጥ ሳይቀር፤ አፍጋኒስታን በእግር ኳስ የምናዉቀዉ አይደለም በእስያ ዉድድሮች አይሳተፍም፣ በአለም ዋንጫ ተሳትፎ አያዉቅም ግን የአፍጋኒስታን ሊግ ዉስጥ ጭምር ዉርርድ ሲደረግ ታያለህ እና ከስፖርቱ ይልቅ ቁማሩ ያደላል”።

በኢትዮጵያ ያለዉ አሁናዊ መልክ አሳሳቢ መሆኑን ከወራት በፊት ያስነበበዉ አለምአቀፉ ተነባቢ መፅሄት ዘ ኢኮኖሚስት ፤ ኢትዮጵያ በቁማር በሽታ ተይዛለች የሚል ርእስን ሰጥቶት ነዉ ለንባብ ባበቃዉ ዘገባ የዉርርድ ጨዋታ የሚሉት ይሄዉ  ከትንሹ 10 ብር እስከ በርካታ ገንዘቦች የሚመደብበት ዉርርድ በማህበረሰቡ ዘንድ ስር የሰደደ ችግርን ይዞ ስለመምጣቱ ነዉ የሚያነሳው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ሶሻል ሳይኮሎጂ 2ኛ አመት የፒኤችዲ ተማሪ እና  በሲቪልሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አማካሪ የሆኑት ቁምነገር ፍቅሬ እንደሚሉት፥ የድርጊት ተደጋጋሚነት ደግሞ ዉጤቱ የከፋ እዛው አዙሮም  የሚጥል ነው።

ቁምነገር ፍቅሬ፥ “ ዉሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነዉ የሚባል ነገር አለ አይደል፤ መጀመሪያ ላይ እንዲሁ እንደቀልድ ትጀምረዋለህ ማቆምም ትችል ነበር ፤ ከዛ በኋላ ግን እያደገ እያደገ ይሄድና ችግር ይሆናል ማለት ነዉ፤ የጤናም ጉዳይ ይሆናል  አንተ ፈልገህ የምትወጣበት ነገር አይሆንም ሌላ እገዛ ያስፈልግሀል የቤተሰብህ፣ የማህበረሰብህ፣ የጤና ተቋማት እገዛ ያስፈልግሀል፤ ማህበራዊም የጤናም ጉዳይ ነው ማለት ነዉ ፤ ስለዚህ እንደታመመ ሰዉ ልትቆጥረዉ ትችላለህ ማለት ነዉ”።

ጎጂ መሆኑን ምናልባት ከእኛ የበለጠ በደንብ ሊገልፀዉ ይችላል ያ ሰዉ ነገር ግን ማቆም የማይችልበት ደረጃ ላይ ይድርሳል”።

በእርግጥም ባለሙያዋ እንደሚሉት እንደ ካርታ እና ሌሎችም አይነት ጨዋታዎች ቁማር ከምንለዉ ስማቸዉ በተጓዳኝ በሀዘን ቤት ባላቸዉ ማህበራዊ ፋይዳ  እናዉቃቸዋለን፤ መሰል ዉርርዶችም መነሻቸዉ ምንም ይሁን ምን ተደጋጋሚነታቸዉ ሱስን ይዘዉ መምጣታቸዉ፤ ከግለሰብ እስከሀገር የሚደርስ ቀዉስን መጥራታቸዉ አይቀርም ።

የዘ ኢኮኖሚስቱ ዘገባ እና ሌሎችም ስለጉዳዩ የሚያዉቁ ይህንኑ አይነት እንቅስቃሴ ቁማር ነዉ ሲሉት፤ ስለመሰል ጉዳዮች ይሁንታዉ የሚጠበቅ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ግን  የዉርርድ ጨዋታ ነዉ በሚል ህጋዊ ፈቃድ እና እዉቅና ሰጥቶታል።

አሁን ወደ 22 የሚጠጉ ድርጅቶችም እየተንቀሳቀሱ ቆይተዋል፤ አሁን አሁን የማህበራዊ ቀዉሱ ብልጭታዎች መታየት ጀምረዋል። ለመሆኑ የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ምንድን ነው፤ ጉዳዩ ከማህበራዊ ቀዉስ በሀገሪቱ እግርኳስ ላይ የሚያሳርፈዉ አሉታዎ ጫናስ የት ይደርሳል ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሎተሪስ ምላሽስ

በቀጣይ ተከታታይ ዘገባዎችን የምንሰራ ይህናል ።

በፀጋዬ ወንድወሰን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.